Translate

Thursday, January 7, 2016

የነጻነት ቀን ቀርባለችና ጸንታችሁ ቁሙ! (እየሩሳሌም ተስፋው — ከቃሊቲ ማጎሪያ ቤት፣ አዲስ አበባ)

እየሩሳሌም ተስፋው (ከቃሊቲ ማጎሪያ ቤት፣ አዲስ አበባ)

እነሆ በጨለማ ቤት ውስጥ ከታጎርን 311 ቀናት ሞሉን፡፡ ጊዜው እንዴት ይሮጣል ባካችሁ? የዛሬ አመት በዚህ ወቅት ከጓደኞቼ ጋር በዝዋይ እስር ቤት የሚገኙትን ጀግኖቻችንን ለመጠየቅና እንኳን አደረሳችሁ ለማለት የገና ዋዜማን በዝዋይ ወህኒ ቤት ተገኝተን ነበር፡፡ ግን ምኞታችን ቅዠት ሆኖ ያሰብነው ሳይሳካ አንድም የፖለቲካ እስረኛ ማግኘት ሳንችል በሩን ተሳልመን ተመለስን፤ መጠየቅ አትችሉም ተብለን፡፡Eyerusalem Tesfaw
የገና ዕለትም እንደለመድነው ከጀግኖቻችን ጋር ለማሳለፍ መጀመሪያ በቂሊንጦ ወህኒ ቤት፣ ቀጥሎ የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች ናቸውና የቃሊቲ ጀግኖቻችን ከእነሱ ጋር በማሳለፍ ለማስታወሻ ይሆነን ዘንድ እዚሁ ቃሊቲ በር ላይ ተሰባስበን ፎቶ ተነሳን፡፡ ያ በዓል ለእኔ እና ለአባሪዎቼ የመጨረሻ በዓላችን ነበር፡፡ ሆኖም በዓሁኑ ሰዓት በዚያ ፎቶ ላይ ተሰባስበን ከተነሳነው ስንት ሰው እንደሆነ በሰፊው እስር ቤት የቀረው እናንተው ማየት ትችላላችሁ፡፡ (ፎቶ ከተገኘ ማለቴ ነው)

ግማሾቻችን ቃሊቲ፣ ግማሾቹ ቂሊንጦ፣ ግማሾቹ ማዕከላዊ፣ ግማሾቹ ሸዋሮቢት ታጉረዋል፤ የቀሩትም ከሀገር ተሰደዋል፣ አንድ ሁለት ቆራጦች ደግሞ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሀገር ቤት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ መጨረሻ! መታሰር አልያም ከሀገር መሰደድ! በቅርቡ የማደንቃቸውና የማከብራቸው ጓደኞቼ ወደ ማዕከላዊ መግባታቸውን ስሰማ በጣም አመመኝ፡፡ በእርግጥ ወያኔ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ መታሰር አዲስ አይደለም፡፡ ከመታሰርም በላይ ወንድማችን ሳሙኤል አወቀ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሏል፤ በኦሮሚያ ያለውን ግድያ የምናውቀው ነው፡፡ ግን እስከመቼ ግፉ ይቀጥላል? እስከመቼስ በዚህ ሁኔታ ጀግኖቻችንን እያስበላን እንቀጠላለን? እስከመቼስ መረጃ ምንጮቻችን የሆኑት ሚዲያዎች ሲታገዱ እንታገሳለን? እስከመቼ በፍርሃት ቆፈን ተቀፍድደን እንቀመጣለን? እስከመቼ እስሩና ግድያው የእኛን ቤት እስኪያንኳኳ እንጠብቃለን?
ለመሆኑ ቆርጠን ተነስተን ወያኔን ታግለን እንዳንጥል ያደረገን ምንድነው? ከአፍሪካ የስልጣኔ እና የነጻነት ፈር ቀዳጅ ተምሳሌት እንዳልነበርን ዛሬ ከጎረቤት ኬንያ እንኳን አንሰን ስንገኝ ምን ይባላል? አዎ በረባ ባረባው ለራሳችን የምንሰጠው ምክንያት ወደኋላ እየጎተተን ይገኛል፡፡ ልጄ፣ ሚስቴ፣ ባሌ፣ ልጄ፣ እናቴ፣ አባቴ…ስንል ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከካርታ ላይ እንዳትጠፋብን እሰጋለሁ፡፡ የኢትዮጵያዊነት የጀግንነት ስሜቱ ወዴት ገባ? እድሜ ልክ በፍርሃት ከመኖር አንድ ቀን በጀግንነት መኖር አይሻልምን? ኸረ ንቃ ወገኔ…ተነስ! በቃ እኔ የምልህ ንቃ ነው!
ይህን የምልህ አንዳንድ የአዲስ አበባ ካድሬዎች በወያኔ ቴሌቪዥን እንደሚሉት አውሮፓ ተቀምጬ አይደለም፡፡ እዚሁ በግፍ እስር ላይ ሆኜ እንጂ! ተነስ የምልህ ፈርቼ በማፈግፈግ ሳይሆን ደፍሬ ከፊት በመቆም ነው፡፡ የጀመርኩት የነጻነት ትግል፣ የነጻነት መንገድ አለና ከዳር አድርስልኝ ነው የምልህ! በአንድ ወቅት የዛን ዘመኑ አሸባሪና የአሁን ዘመኑ የሰላም ኖቬል ተሸላሚ ኔልሰን ማንዴላ (ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልንና) እንዲህ ብለው ነበር፤ ‹‹ማንኛውም ህዝብ ሁለት ምርጫ ፊቱ ላይ የሚደቀንበት ጊዜ ይመጣል፡፡ እጅ መስጠት ወይም መሳሪያ ማንሳት? እኛም ሁለተኛውን ምርጫ እንድንመርጥ ተገድደናል›› ብለው ነበር፡፡ እኔም ኢትዮጵያዊነት አልደፈርም፣ አትንኩኝ ባይነት መሆኑን ተረድቼዋለሁና፣ እጅ መስጠት እንኳን ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ገብቶኛል ለምለው ይቅርና ለአንድ ጨቅላ ህጻን ልጅ እጅ መስጠት ማለት ሞት ነውና ልክ እንደ ማንዴላ ሁለተኛውን ምርጫ እንድመርጥ ተገድጃለሁ፣…መሳሪያ ማንሳት!
ምንም እንኳ አሁን ላይ በወያኔ እጅ ወድቄ በዚህ ጨለማ ወህኒ ቤት ብገኝም ራዕዬ ትልቅ ነውና ብዙ በመንገዴ እየሄደበት ይገኛል፡፡ አዎ ዛሬ አካሌ እዚህ ቢገኝም ልቤ ባህርን ተሻግሮ ኤርትራ በርሃ ውስጥ ከጀግኖቹ መንደር ይገኛል፤ ወደ ኢትዮጵያ ከሚገሰግሱት ከነዚያ ልበ-ሙሉዎች ጋር የእኔ ልብ!
በመጨረሻም፣ ማንም ሰው ጀግና ነሽ፣ ጎበዝ ነሽ አይበለኝ! እኔ በሴትነቴ የጀመርኩትን እናንተም ተከተሉኝ፡፡ ልብ ከቆረጠ ሊገታው የሚችለው ምንም ኃይል የለምና! በዚያ በስቃይ ቤት ከማንም ሳትገናኙ መምሸቱንም መንጋቱንም ለምርመራ ስትወጡ ብቻ እያያችሁ በዓሉን የምታሳልፉት የምወዳችሁ ጓደኞቼ አይዟችሁ በርቱልኝ እላለሁ! የማያልፍ የለም!! የነጻነት ጊዜ ቀርባለችና ጸንታችሁ በአቋም ቁሙ! የኢትዮጵያ አምላክ ከእናንተ ጋራ ይሁን!!

No comments:

Post a Comment