Translate

Sunday, January 24, 2016

ርዕዮት ሆይ! ወኔ ቢሶቹን “እንካ መቀኔቴን – ቀበቶህን ስጠኝ” ብለሽ ገስጭልን!

አዜብ ጌታቸው

Ethiopian heroine journalist Reeyot Alemu
አቅም በፈቀደ መጠን በየጊዜው በሃገራችን ወቅታዊ ሁነቶችና ክስተቶች ዙሪያ የተሰማኝን ለመግለጽ ስሞክር ቆይቻለሁ።ታዲያ በእያንዳንዱ ጽሁፍ ላይ በርካታ አስተያየቶች ይደርሱኛል።አብዛኞቹ አበረታች፤ ጥቂቶቹም አርበትባች። አርበትባች ስል ማስፈራራት መሞከራቸውን ለመግለጽ ያህል እንጂ ተርበተበትኩ ማለቴ እንዳልሆነ ይጠፋችኋል አልልም። “እንኳን ለሙቅ ለገንፎ አልደነግጥ አሉ…”። መዳፋቸው ውስጥ ሆና ያርበተበታቻቸውን የርዕዮት ዓለሙን ገድልና ጀግንነት እያየሁ ! እየሰማሁ! እኔ ከ4 ኪሎ ቤተ መንግስት (ቤተ መጥምጥ) በስንት ሺህ ማይልስ ርቀት ላይ ሆኜ እንዴት ልርበተበት? ያውም በኤሜል? እ ተ ተ ተ ተ…. !

አደራ! ራሴን ከርዕዮት ጋር ማመሳሰሌ መስሏችሁ ወዴት ጠጋ ጠጋ..? እንዳትሉኝ። በፍጹም! ደግሞስ እንዴት ልንመሳሰል እንችላለን? እኔ በሪሞት የምቧጥጥ እሷ ገዳዮቹን በአካል የምትጋፈጥ፡፡
የዛሬው ጽሁፌ በምን ላይ እንደሚያጠነጥን ፍንጭ ያገኛችሁ ይመስለኛል። አዎ! የዛሬው ትኩረቴ በዚኽቺው ጀግና እንስት ገድል ላይ ነው ።
በርግጥ ርዕዮት እጇ በወያኔ አፋኞች ከተያዘበት ግዜ ጀምሮ ያሳለፈቺውን ስቃይና ታሳይ የነበረውን ጽናት እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ላለፉት 4 -5 አመታት ስከታተል በመቆይቴ ለሷ ያለኝ ክብርና አድናቆት የቆየ ነው።ይሁንና በውስጤ የገዘፈውን አድናቆትና ክብር አውጥቼ ለመግለጽ የተነሳሳሁት ግን ሰሞኑን በኢሳት ከሲሳይ አጌና (በርባሪው ጋዜጠኛ) ጋር ያደረገቺውን በሁለት ክፍል የቀረበ ቃለ መጠይቅ ካደመጥኩ በኋላ ነው።
ከሁሉ አስቀድሜ ግን የአተራረክ ብቃቷ እጅግ እጅግ በጣም እንዳስደነቀኝ ሳልገልጽ አላልፍም። ድሮስ መምህርነትና ጋዜጠኝነትን መሰል ሙያ አጣምራ ይዛ… እንደምትሉ እገምታለሁ። ጋዜጠኛ ሲሳይ እስከዛሬ ካነጋገራቸው እንግዶች ሁሉ ስራውን ያቀለለችለት እንግዳ ርዕዮት ነች ብል፤ አጋነንሽ ወይም የጾታ አድሎ ነው እንደማልባል ተስፋ አደርጋለሁ። ወደ ዓብይ ጉዳዪ ልመለስ።
በተለምዶ የጀግና ባህሪ፤ ብዙ የማይፈክር ወይም ብዙ የማይናገር፤ አዘኔታን ወይም ምህረትን ከማንም የማይጠብቅ፤ የተበደልኩ ሮሮ የማያበዛ ነው ይባላል፡፡ አባባሉ እውነት አለው ።ከርዕዮት ቃለ መጠይቅም የተረዳሁት ይህንኑ ነው።
አስተውላችሁ ከሆነ ርዕዮት ባደርገቺው ከሁለት ሰአታት በላይ በዘለቀው ቃለ-መጠይቅ ውስጥ ከአራት አመታት በላይ የቆየችበትን ስቃይ፤ የተፈጸመባትን ግፍና በደል… ቁብ ሳትሰጥ የፍትህ ስርዓቱን ዝቅጠት በሚያሳይ መልኩ ብቻ ነበር የምትተርከው። ጀግና ሮሮ አያበዛም። ጀግና እንባውን በወኔው እንጂ የሚያብስው ፤ በደሉን በገድሉ እንጂ የሚረሳው፤ ማንም በአዘኔታ ከንፈሩን እንዲመጥለት አይሻም።
ጀግና ነጻነቱን ከጠላቱ እጅ ፍልቅቆ እንጂ የሚወስዳት በምህረት አይቀበላትም። ርዕዮትም ነጻነቷን በምህረት ሳይሆን አፍንጫቸውን ሰንጋ ከእጃቸው ፈልቅቃ ወሰደች። ለ24 አመታት የቆየውን የወያኔ እስር ቤት “የሰጥቶ መቀበል” (ይቅርታ ተቀብሎ ምህረት መስጠት) ስልት በጽናት አመከነች።
ጀግና በራሱ እንዲደርስ የማይሻውን በሰው ላይ አይፈጽምም፡፡ ርዕዮትም በንጹሃን ሰዎች ላይ መስክረሽ ነጻ እንልቀቅሽ ስትባል፤ “የለም በንጹሃን ላይ መስክሬ ነጻ ከምወጣ እኔኑ ክሰሱኝ” ብላ ጸናች።
በዋናነት ጀግና ፍርሃት አያውቅም። አዎ! አፋኞቹ የፈጠራ ክሱን ለማዘጋጀት ግንቦት 7 እንበለሽ? ኦነግ እንበልሽ? በሚል ላቀረቡላት የፌዝ ጥያቄ ርዕዮት የሰጠቺው መልስ፤ “የፈለጋችሁትን በሉኝ ብቻ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ አትበሉኝ!” የሚል አፈር ያስገባቸውን መልስ ነበር።
ውድ አንባቢያን እስኪ ንባቡን ለደቂቃ ቆም አድርጉና ይህን አስቡ፡..
ገለው እንኳ ጭካኔያቸው አላረካ ሲላቸው ሬሳውን በሰደፍ የሚደበድቡ አረመኔዎች እጅ ገብታ በእንዲህ አይነት ድፍረት ምላሽ የሰጠችን ነፍስ በህሊናችሁ አስቡና ራሳችሁን በሷ ጫማ ከታችሁ ተመልከቱ! ታደርጉታላችሁ? አዎ! ርዕዮትን ልዩ ጀግና የሚያደርጋት ይኽው ነው። ልዩ የጭካኔ አቅም ያላቸውን ጠላቶቿን መጋፈጧ። ብሎም ማንበርከኳ!
እዚህ ላይ አንድ ሌላ ነገር ታወሰኝ፦
በ1997 ምርጫ ማግስት ማለትም በግንቦት 7 ምስረታ ዋዜማ፤ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አንድ አወያይ ጽሁፍ አቅርበው ነበር፡፡ ጽሁፉ ያለፈውን የሰላማዊ ትግል ሂደትና ውጤት የገመገመና መጪው የትግል አቅጣጫ ምን መሆን እንዳለበት ያመላከተ እንደነበር አስታውሳለሁ። የአቶ አንዳርጋቸው ጽሁፍ ወያኔ ሰላማዊ የሚባል ነገር የማይገባው መሆኑን አሳይተው፤ በቀጣይ አመጽንም የሚያካትት ሁለገብ የትግል ስልትን መከተል እንደሚገባ አስረግጠው ያስገነዘቡበት ነበር።
በዚያ ወቅት ታዲያ “ሰላማዊ ትግሉ መቼ ተነካና ?” የሚሉ ወገኖች የአቶ አንዳርጋቸውን ሃሳብ በጽኑ ተቃወሙ። መች ተነካና ያሉትን የሰላማዊ ትግል አይነት እየዘረዘሩ አቀረቡ፤ ጋንዲንም ማርቲን ሉተር ኪንግንም ከመቃብር ቤት ለምስክርነት ጠሩ። ዳግም ወደ ጦርነት አንገባም ፤ በሰላማዊ ትግል ቆርበናል ያሉ ሁሉ አቧራውን አጨሱት።
አቶ አንዳርጋቸው “ሰላማዊ ትግሉ መቼ ተነካና ?” በሚል የተነሳባቸውን ተቃውሞ አስመልክቶ በዛው ሰሞን ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሰጡት ምላሽ ታዲያ መቼም የምረሳው አይደለም።
አቶ አንዳርጋቸው የሰጡት መልስ፦ የጋንዲንና የማርቲን ሉተር ኪንግን የትግል ተመክሮ እየጠቀሱ ሰላማዊው ትግል መቼ ተነካና የሚሉ ወገኖች አንድ የሳቱት ነገር አለ። የጋንዲም ሆነ የማርቲን ጠላቶች የሰለጠኑ ጠላቶች ነበሩ፡፤ ጋንዲ የረሃብ አድማ ሲያደርግ እንዳይሞትባቸው የሚጨነቁ፤ ከውሃ ጋር ፈሳሽ ምግብ(ግሉኮስ) ደብቀው እየሰጡ ህይወቱን ለማትረፍ ይሞክሩ የነበሩ ናቸው። የኛ ጠላት ወያኔ ግን የሰለጠነ ጠላት አይደለም። ሁሉንም ጥያቄ በጠመንጃ አፈሙዝ ለመመለስ የቆረጠ፤ ባህሪውም ፍጥረቱም ሰላማዊ መንገድ እንዲከተል የማይፈቅድለት ጠላት ነው። ስለዚህ የኛም ቀጣዩ የትግል ስልት መነደፍ ያለበት ከወያኔ ድርጅታዊ ባህሪና ተፈጥሮ በመነሳት እንጂ ከነጋንዲ ተመክሮና ታሪክ አይደለም፡፡ የሚል መልስ ነበር የሰጡት (ቃል በቃል ሳይሆን ፍሬ ሃሳቡን በራሴው መንገድ ነው የገለጽኩት) ከአስራ ሃንድ አመት በፊት “ሰላማዊ ትግሉ መች ተነካና ?” በሚል የሰላማዊ ትግል ስልትን ጥራዝ እየገለጡ አቶ አንዳርጋቸውን ሲሞግቱ የነበሩ ወገኖች ዛሬ ላይ ቆመው ሲያስቡት የአቶ አንዳርጋቸው አርቆ አስተዋይነት ሊታያቸው ግድ ይላል።
አሁንም ወደ ተነሳሁበት ልመለስ፦ የአቶ አንዳርጋቸውን ምላሽ እዚህ ላይ መጠቀስ ያስፈለገኝ ፤ የዛሬዋ ተዘካሪ ጀግና የርዕዮት አለሙ ገድል ከወርቅ ጸዳል ፈክቶ እንዲታይ ግድ የሚለው፤ ካልሰለጠኑ ጠላቶች ጋር ታግላ በማሸነፏ መሆኑን ለማሳየት ነው። ጨካኝ ጠላትን ለመታገል ብርቱ ጽናት ያስፈልጋል።ለማሸነፍ ደግሞ ጀግንነት።
አዎ! ወያኔ ፈሪ ነው! ፈሪ ደግሞ ፎካሪና ጨካኝ ነው።
የፈሪ ነገር ሲነሳ ባለ ራዕይው መሪ ፈሪ እንደነበሩ አብሮ አደግ ጓዶቻቸው ያጋለጧቸው ነገር ትዝ አለኝ፡፤ ይቅርታ ነፍሳቸውን ይማርና ማለት ነበረብኝ ለካ? (ዳሩ የላይኛው ጌታ እንደሳቸው የይቅርታ ፎርም አስሞልቶ አይደል ምህረት የሚሰጠው። በስራ ሚዛን እንጂ፡ .. እንደስራቸው! ..ማለቱ ይሻላል ) እናም የባለ ራዕይው መሪ ፍርሃት ወደር አልነበረውም አሉ። ፈሪ ፎካሪ አይደል፤ ሲፎክሩም አቻ የላቸውም። ባጠቃላይ ተፈጥሯቸው፦
የሞተ ባገኝ እሱን አያርገኝ!
የቆመ ሳገኝ ፈሴም አይገኝ! አይነት ነበር አሉ አብሮ አደጎቻቸው።
ፈሪ ባይኖር ኖሮ ጀግና አይኖርም ነበር። ፍርሃት የሚባል ነገር ባይኖር ጀግንነትም ትርጉም ባልኖረው ነበር፡፤ ለዚህ ነው
የርዕዮትን ገድል እያወራሁ ድንገት ወደ ባለ ራዕይው ማንነት የገባሁት።ለንፅፅር ።
ፈሪውን እዚህ ላይ ላውርደውና ወደ ጀግናዋ ልመለስ። ጀግና ሲወደስ ደስ ደስ ይላል። ርዕዮት በእሳት የተፈተነች ወርቅ ነች።
ከሃገር ቤት በብዙ ሺህ ማይልስ ርቆ በውጭው አለም እየኖረ የወያኔን መንግስት ለመቃወም በሚጠራ ሰልፍ ላይ ሰፌድ የሚያህል ባርኔጣና ጥቁር መነጽር ደንቅሮ አዩኝ አላዩኝ እያለ በፍርሃት የሚርደውን ዜጋ ስናስብ የርዕዮት ገድል ገዝፎ ሊታየን ግድ ይላል።
ለኩርማን መሬት ብሎ የወገኑን ስቃይ አይቶ እንዳላየ በሚያልፈው ስግብግብ ኢትዮጵያዊ ተብዬ ተግባር የሚያዝነው ህዝባችን በርዕዮት መሰል ጀግኖች መስዋእትነት ይጽናናል።
በርዕዮት ጀግንነት የተደመሙ! ወገኖች የዘመናችን ጣይቱ ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸውላታል፡፤ ይገባታል! ጣይቱ ባህር ተሻግሮ የመጣን ፋሽሽት አሳፍራ መለሰች። ርዕዮት ደግሞ ወንዝ አፈራሹን ፋሽሽት ብቻዋን! አንበረከከች።
በነገራችን ላይ በታሪክ ጎልቶ የሚጠቀሰው የእቴጌ ጣይቱ ጀግንነት ይሁን እንጂ በተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ውስጥ ሳጋ እየገቡ የተጠቀሱ ሌሎችም በርካታ ጀግና እናቶች ነበሩ። ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት ተብሎ ጦርነት ሲታወጅ፤ ለሰራዊቱ ስንቅ የማዘጋጀቱ ኃላፊነት መሉ ለሙሉ የእናቶች ነበር።
ደረቅ ስንቅ ከማዘጋጀት ባሻገር አብረው ዘምተው ከተዋጊው ኋላ እንጀራ እየጋገሩ ወጥ እየሰሩ ሰራዊቱን ይመግቡ ነበር። ይህ ብቻም አይደለም። እናቶቻችን በውጊያ ወቅት ፈርቶ የሚያፈገፍግ ወታደር ሲመለከቱ መቀነታቸውን እየፈቱ “እንካ መቀኔቴን – ዝናርክን ፍታና ለኔ ስጠኝ” በማለት እየገሰጹ ፊቱን ወደ ጠላት አዙሮ በወኔ እንዲዋጋ ያበረታቱ እንደነበርም ተጽፏል፡፡
ንጉስ ክተት ሰራዊት ብሎ ጦርነት ሲያውጅ እያንዳንዱ ለአቅመ አዳም የደረሰ ሰው በራሱ ስንቅና ትጥቅ ለዘመቻ ይዘጋጃል። አልጋ የያዘ በሽተኛ ካልሆነ በስተቀር ከንጉስ ሰራዊት ተነጥሎ የሚቀር ሰው፤ እንደ ሰው አይቆጠርም።ሚስቱም ባል አታደርገውም።ወንዶች የዋሉበት ያልዋለ ባል ለሚስቱ ማፈሪያ ነው። አባትም ከሆነ ለልጆቹ መሰደቢያ ነው።
ተወዳጁ የባህል ዘፈን አቀንቃኝ ባህሩ ቀኜ፡
ገዳይ ገዳይ ያልሽው ባልሽ ሰው አይገድል፤
አርሶ ያብላሽ እንጂ ሆድሽ እንዳይጎድል፤
ሲል በዜማ የቋጠራቸው ስንኞች ይህኑ የሚያሳዩ ናቸው። ህይወትን ከፍሎ ሃገርን ማቆየት የሰውነት መገለጫ ነበር ። ዛሬ ደግሞ በተቃራኒው አገርን አሳልፎ ሰጥቶ(ችላ ብሎ) ህይወትን ማቆየት ተለመደ፡፡ የርዕዮት ጀግንነትም በበርሃ ውስጥ እንደ በቀለች ጽጌሬዳ ብርቅ የሚሆነውም ለዚህ ነው።
ውድ አንባቢያን ጽሁፌን ልቋጭ ነው፦ ከዚያ በፊት ግን ይህቺ መልዕክት ለርዕዮት አድርሼ እመለሳለሁ ታገሱኝ።
ውድ እህቴ ርዕዮት ሆይ! ከሁሉ አስቀድሜ ለአራት አመታት የተሸከምሺውን የመከራ ቀንበር ሰባብረሽ፤ እንኳን ከነክብርሽ ለነጻነት በቃሽ እላለሁ።
ውድ እህቴ ርዕዮት! በታሪክ ሲዘከር የሚኖር ጀግንነት ፈጽመሻል፡፡ የአርአያነትሽ ፋይዳም ግዙፍ ነው።
ጽናትሽ አንቺ ያሳለፍሺውን ስቃይ እያሳለፉ ላሉት የህሊና ዕስረኞች የመንፈስ ብርታት ነው።
ቁርጠኝነትሽ ለህዝብ ነጻነት ለሚታገለው ወገን ጉልበት ነው።
መስዋዕትነትሽ ለሆዳቸው አድረው ለሚልከሰከሱ ባንዶች የህሊና ቁስል ነው።
እንስትነትሽ በጓዳቸው ከትመው ሃገራቸውን ለረሱ እህቶቻችን ማነቃቂያ ደውል ነው።
ድልሽ የነጻነት ቀን መቅረቡን አመላካች ተስፋ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ከአራት አመታት ስቃይ በኋላም እረፍት ስታፈልጊ ብረት አንስተው ዘረኛውን መንግስት ለመጣል የተሰለፉ ወገኖችን መቀላቀልሽ በራሱ፤ በፍርሃትም ሆነ በለዘብተኝነት እጁን አጣጥፎ የተቀመጠውን ወገን “እንካ መቀኔቴን – ዝናርክን ፍታና ለኔ ስጠኝ” ብለሽ የገሰጽሽበት ድንቅ ተግባር ነውና ልትኮሪ ይገባሻል። ወኔ ቢሶቹ ለዝናር ባይታደሉም ቀበቶ አያጡምና “እንካ መቀኔቴን – ቀበቶህና ስጠኝ”ብለሽ ገስጭልን። ፈሪን መገሰጽ በጀግና ያምራል። ፈተናሽን በጽናት እንድትወጪ የደገፉሽ ወላጆችሽና ቤተሰቦችሽ በሙሉ ምስጋናና ክብር ይገባቸዋል።
ውድ አንባቢያን በጣም ይቅርታ! አቆየኋችሁ፡ የርዕዮት ገድል ብዙ ቦታ ውስጥ ከተተኝና ጽሁፌ ረዘመ። በትዕግስት አንብባችሁ እዚህች ድረስ ከደረሳችሁ፡፤ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው፡፤ እንዲሁ ደግሞ ጊዜ በሚያፈራው ሌላ ጉዳይ የሚሰማኝን ጣጥፌ እስከምንገናኝ ሰላም ሁኑልኝ።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
azebgeta@gmail.com

No comments:

Post a Comment