አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ለረጂም ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሳትፏቸው ይታወቃሉ፤ በተለይም የኦሮሞን ህዝብ መብት እናስከብራለን ብለው የፖለቲካ ፓርቲ መስርተው ከታገሉት ሰዎች መካከል ከፊተኞቹ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ቡልቻ አሁን ስላሉበት የፖለቲካ ተሳትፏቸውና ስለተለያዩ አንኳር ሀገራዊ ጉዳዮች ከጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ጋር ቆይታ አድርገዋል፤ እንዲህ ይቀርባል፡-
ነገረ ኢትዮጵያ፡- አቶ ቡልቻ በተለያዩ መድረኮች ላይ በፖለቲካ ተሳትፎዎ ነው የሚታወቁት፤ ነገር ግን አሁን ላይ ከፓርቲ ፖለቲካ ተሳትፎ የራቁ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ወቅት ስላልዎት የፖለቲካ ተሳትፎዎ በአጭሩ ቢነግሩኝ?
አቶ ቡልቻ፡- እኔ ከመድረክ የገባሁት የኦፌኮ መሪ ሆኜ ነው፡፡ አሁን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) እስኪ ወጣቶቹ ይስሩ፣ እነሱ ሲሰሩ የሚቻለኝን እርዳታ አደርጋለሁ ብዬ በራሴ ፈቃድ ከፓርቲ ፖለቲካ ወጥቻለሁ፡፡ ‹‹Retire›› አድርጌያለሁ፡፡ እግዚአብሄር ይመስገን ጤናማ ነኝ፡፡ በእድሜየ በኩል 83 አመቴ ነው፡፡ በትምህርትም ሆነ በተፈጥሮ ስጦታ ትልቅ አቅም ያላቸው ልጆች ስላሉ እኔ በዚህ እድሜዬ መድከም የለብኝም ብዬ ነው የለቀቅኩት፡፡