“ … ወታደር ባለመሆኔ የጦርነቱን ውሎ ማተት አያምርብኝም፡፡ ያም ሆኖ የአድዋ ድል ዛሬ ብርቅ በሆኑብን ሁለት እሴቶች ረድኤት የተገኘ ይመስለኛል፡፡ እኒህ ሁለት እሴቶች መተባበርና መደማመጥ ናቸው፡፡ ጣልያኖቹ በጊዜው ወደ ጦርነት ሲገቡ ተስፋቸውን የጣሉት በመድፍና በጠመንጃቸው ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ዝነኛ በነበሩበት የውስጥ መቆራቆስ ላይ ነው፡፡ የትግራይ ቅልጥም ሲመታ ሸዋ ያነክሳል ብለው አላሰቡም፡፡ በርግጥም በክፍለ ሀገሮች ውስጥ የተለያዩ ሽኩቻዎች ነበሩ፡፡ እኒህን ሽኩቻዎች አስረስቶ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ለአንድ አላማ ማሠለፍ ምኒልክነትን ይጠይቃል፡፡
“መደማመጥ ያልሁትን ላሳይ፡፡ አባ ዳኘው ከዛሬው የይስሙላ ፓርላማችን በተሻለ ሁኔታ ለልዩነቶች ቦታ የሚሰጥ ተንቀሳቃሽ ምክር ቤት በጦርነቱ ወቅት መፍጠር ችለዋል፡፡ ፀሐፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ በውጊያው ዋዜማ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ይገልፁታል
‘… አፄ ሚኒልክም በበነጋው ሰራዊቱን የቀኙን በቀኝ፣ የግራውን በግራ አሰልፈው ነጋሪትዋን እያስመቱ ወደሱ ተጓዙ፡፡ ኢጣሊያኖችም ዘበኛው ሲመጣ ባዩ ጊዜ ተመልሰው ወደ እርዳቸው ገብተው ተኙ፡፡
ከዚህ በኋላ ሰራዊቱም እንደ ኤሊ ስንመጣበት ከድንጋይ ይገባል፤ ስንመለስ ይወጣል፤ እንዲህ አርጐ ሊጫወትብን ነውን? ብሎ እጅግ አጥብቆ ተናደደ፡፡ መኳንንቶቹም ተሰብስበው ከዚህ ሰፍረን አድረን በማለዳ እዚያው ካሉበት ከርዱ ድረስ ሄደን እንዋጋለን ብለው መከሩ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም እሺ ብለው ድንኳኑን ለማስመጣት አዘዙ፡፡
ይህ ምክር ካለቀ በኋላ የትግሬው ገዢ ራስ መንገሻ ተሰልፎ በፈረስ ሆኖ መጣ፡፡ እሱም ይህ ምክር እንዳለቀ ባዬ ጊዜ አንድ ነገር ልናገር ይፍቀዱልኝ ብሎ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ቀርቦ እንዲህ አለ፡፡ እንደ ተርታ ነገር ካልሆነ ስፍራ ሄደን ልናስፈጀው ነውን? አለ፡፡ ይህ ምክር የተስማማ ምክር ሆነ፡፡ አፄ ምኒልክም ተመልሰው ከድንኳንዋ ከገቡ በኋላ እንዲህ አሉ፡፡ እንግዲህ ከሰፈሬ ወጥቶ ተኩስ አልጀመረ ባይኔ ካላየሁት ተሰልፌ አልወጣም፡፡’
“ፀሐፌ ትእዛዝ ያቀረቡትን ዘገባ ወደ ዘመናዊ አማርኛ አሳጥሬ ሳዛውረው የሚከተለውን ይመስላል፡፡
“እንደተመለከተው አጤ ምኒልክ ልዩ ልዩ ሐሳቦችን ለማዳመጥና አወዳድረው የነጠረውን ሐሳብ ለማስፈፀም ዝግጁ ነበሩ፡፡ በአራት ነጥብ የታጠረ ግትርነት አልነበረባቸውም፡፡
“ሾፐናወር የተባለ የጀርመን አገር ፈላስፋ ከአድዋ ሠላሳ አምስት አመት አስቀድሞ “ከጥንት ግብፃውያንና ከህንዶች ውጭ ያለው ታላቅ የስልጣኔ ፍሬ ሁሉ በነጮች ጥረት ውጤት ነው፡፡ ከጥቁር ህዝቦች መካከል እንኳ የገዢነትን ስልጣን የሚይዙት በቀለም ፈካ ያሉት ናቸው” ብሎ ነበር፡፡ ያጤ ምኒልክ ፊት ይህንን ንድፈ ሐሳብ በይፋ ለማስተባበል የተፈጠረ አይመስልም?”
በዕውቀቱ ስዩም፤
ምንጭ፡ ፍትህ፤ ቅጽ 5፣ ቁጥር 177፤ የካቲት 23፤2004ዓም
No comments:
Post a Comment