በዓለም ዉድድር አለ። ዉድድሩ በህዝቦች መካከል ነው። ህዝቦች ዉድድሩን ለማሸነፍ አብሮነትን ይፈልጋሉ። በአብሮነት የራሳቸው ደህንነትና ጥቅም ማስከበር ይሻሉ። ደህንነታቸውንና ጥቅማቸው ለማስከበር ሀገር ይመሰርታሉ። ሀገር መስርተው በመንግስት ይወከላሉ። የመንግስት ተግባር ታድያ የህዝቡን ጥቅምና ደህንነት መጠበቅ ነው። በዚሁ መሰረት መንግስት የህዝቦች ተወካይ ጠበቃ መሆን ይጠበቅበታል።
የህዝቦች ወኪል (ጠበቃ) ለመሆን መንግስት በተለያዩ ሀገሮች ኤምባሲ ይከፍታል። የኤምባሲው ሰራተኞች የሚወክሉትን ህዝብ ጥቅምና ደህንነት ይጠብቃሉ፣ ያስጠብቃሉ። ለዚሁ ተግባራቸው ሲባል ህዝብ ደሞዛቸውን ይከፍላቸዋል። ደሞዛቸው የሚከፈላቸው ከመንግስት ካዝና ነው። የመንግስት ገንዘብ የሚሰበሰበው ከህዝብ ነው፤ በግብር መልክ።
የኢትዮጵያ መንግስትም (መንግስት ልበለው) ከህዝብ ኪስ የሚከፈሉ የኤምባሲ ሰራተኞች አሉት። በተለያዩ ሀገሮች ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰራተኞች በህዝብ ገንዘብ እየተዳደሩ የሚከፍላቸውን ህዝብ የሚበድሉ መሆናቸው እናውቃለን። ዛሬ ትኩረቴ የሳበ ግን በካርቱም ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው።
ካርቱም የሚገኙ ጓደኞቼ እንደላኩልኝ ከሆነ የኢትዮጵያ ኤምባሲ (በካርቱም) ሰራተኞች በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባር ተሰማርተው ኢትዮጵያውያንን አደጋ ዉስጥ እየጣሉ ይገኛሉ። የሰዎች ደህንነት ከመጠበቅ ይልቅ ሰዎችን አደጋ ዉስጥ ማስገባት ምን ይሉታል? የመንግስት አካላት ወንጀልን ከመከላከል ይልቅ ቁማርተኞች ሲሆኑ ምን ማድረግ ይቻላል?!
የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰራተኞች ሱዳን ዉስጥ የሚቸገሩ ዜጎቻችንን ደህንነት ከመከታተል ይልቅ ከሱዳን መንግስት ጋር በመተባበር ኢትዮጵያውያን እስርቤት ይከታሉ። እስካሁን ድረስ በሱዳን ብዙ ኢትዮጵያውያን ያለ ምንም ጠያቂ በወህኒቤቶች እየማቀቁ ነው። የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰራተኞች በሱዳን ሀገር የሚደርስባቸው ችግር፣ እስር፣ እንግልት እያወቁ በሰዎች ንግድ መሰማራታቸው ይገርማል። የኤምባሲው ሰራተኞች በሀገራቸው ሰዎች ንግድ ነው የተሰማሩ።
በሱዳን ያሉ ኢትዮጵያውያን መንግስት እንደሌላቸው (መንግስት አልባ እንደሆኑ) ነው የሚቆጠረው። “ሑዳ” በሚባል ወህኒቤት 35 ጠያቂ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን አሉ። እነዚህ እስረኞች ያለ ምንም የፍርድቤት ዉሳኔ የተያዙና ከ8-12 ዓመት በወህኒቤቱ የቆዩ ናቸው። ተሰቅለው የተገደሉም መዓት ናቸው። በሱዳን የኢትዮጵያውያን ህይወት ርካሽ ነው። መስከረም አያሌው የተባለችም በሰባት ሱዳናውያን መደፈሯ ይታወሳል።
ኢትዮጵያውያን መንግስት አልባ (stateless) ሁነው ሲሰቃዩ የኤምባሲው ሰራተኞች ግን ሰዎች እየገዙና እየሸጡ (በሰዎች ንግድ ተሰማርተው) ገንዘብ ይሰበስባሉ። ዘመናዊ መንግስታዊ የንግድ ባርያ መሆኑ ነው።
ኢትዮጵያውያን ክብራችንን የምናስመልስበት ግዜ ሩቅ አይሆንም። አቶ መሐመድ ቱፋና አቶ በላቸው ግን ተግባራቹሁ ሁሉ እየተከታተልነው እንገኛለን።
It is so!!!
No comments:
Post a Comment