Translate

Tuesday, January 24, 2017

ቀዝቃዛዉ ጥምቀትና የበረከት ስምዖን “ግብረኃይል” በጎንደር

ቀዝቃዛዉ ጥምቀትና የበረከት ስምዖን “ግብረኃይል” በጎንደር


ጥምቀትን ያለ ጎንደር ማሰብ የሚቻል አይደለም። ጥምቀት ከኃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባህላዊ ገጽታ የሚንጸባረቅበት ጉምቱ የአደባባይ በዓል ነበር። የጎንደር ጥምቀት እንኳን ለቱሪስቶች ለቀየዉ ነዋሪዎችም ታይቶ የሚጠገብ አልነበረም። በየዓመቱ በአማካይ 1500 የሚደርሱ ቱሪስቶች ከተለያዮ የአለማችን ክፍሎች ተሰባስበዉ ጎንደር ላይ ይከትሙ ነበር። ታይቶ የማይጠገበዉን የጥምቀት ትዕይንት ከከተራ እስከ ሚካኤል ንግስ ድረስ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚጎበኙት የዉጭ አገር ቱሪስቶች ብቻ ሳይሆን የአገር ዉስጥ ጎብኝዎችም በስፋት ይታደሙ ነበር። “ነበር እንዲህ ቅርብ ኑሯል ለካ” እንድትል ንግስት ጣይቱ ብጡል፤ የ2009 የጥምቀት በዓል አከባበር በጎንደር፡-ያን አስደማሚ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ትዕይንት “ነበር” አድርጎት አልፏል።

የወልቃት የአማራ ማንነት ጥያቄን አስታኮ የተቀሰቀሰዉ ህዝባዊ አመጽ በቀደመዉ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ከተፈጠረዉ አመጽ ጋር እየተመጋገበ ኢትዮጵያ ሳልሳዊ አብዮት እንድታስተናግድ እያስማጣት ይገኛል።አብዮቱ ይወለዳል ወይስ ይዘገያል የሚለዉ ጥያቄ ሌላ ጥያቄ ነዉ። ይሁንና በአገሪቱ በተለያዮ የክልል ከተሞች የጠቀሰቀሰዉን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ የገዥዉ መደብ የግድያና የአፈና እጆች ረዘም ብለዉ ታይተዋል። ይህን ተከትሎ የታወጀዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አገሪቱን ቅርቃር ውስጥ ከቷታል። የዚህ ነጸብራቅ ዉጤት የሆነዉ የጎንደር ጥምቀት እጅግ ቀዝቃዛ በሆነ ድባብ “ተከብሮ” አልፏል።
የበረከት ስምዖን ግብረኃይል
የ2009 የመስቀል በዓል ለአገሪቱ የፖለቲካ ታዛቢዎች በሚደንቅ መልኩ ለገዥዉ መደብ ቁንጮዎች ደግሞ በሚያስበረግግ ሁኔታ በህዝባዊ አድማ ጎንደር ላይ በዓሉ በአደባባይ ሳይከበር እንደቀረ የሚታወስ ነዉ። ይህ ህዝባዊ ህብረት ያስበረገገዉ የገዥዉ መደብ ቁንጮ ህዝባዊ አድማዉ የጥምቀት በዓል ላይ እንዳይደገም በመስጋት በህዳር ወር የመጀመሪያ ሳምንት በበረከት ስምዖን አደራጅነት አንድ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ተደረገ። ይኅዉ ግብረ ኃይል ከኮማንድ ፖስቱ ጋር እየተናበበ ለጥምቀት በዓል አከባበር አስፈላጊ ቅድመ ሆኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ተጠምዶ ከረመ። ይኅዉ ግብረ ኃይል በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ መንግስታዊ መዋቅር ምንም አይነት ሥልጣን ለሌለዉ በረከት ስምዖን በየሳምንቱ ሪፖርት ያቀርብ ነበር። የግብረ ኃይሉ ዓላማ የጥምቀት በዓል እንዳይከበር “እንቅፋት” የሚፈጥሩ ህዝባዊ ኃይሎችን እየመነጠረ ለኮማንድ ፖስቱ አሳልፎ የሚሰጥ ሲሆን፤ ይኄዉ ግብረ ኃይል ከጥምቀት በዓል በኋላ እንዲበተን ታስቦ የተደራጀ ነዉ።
የግብረ ኃይሉ አወቃቀር ከጎንደር ዩኒቨርስቲ፣ ከመምህራን ኮሌጅ፣ ከቴክኒክና ሙያ፤ ከሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ ከክፍለ ከተማ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊዎች፣ የገዥዉ መደብ ክንፍ ከሆኑት የሊግና ፎረም ማህበራት አመራሮች እንዲሁም የሰሜን ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ዉስጥ ሰርገዉ የገቡ የገዥዉ መደብ ተነጣፊ የቤተ ክህነት ቁንጮ ሰዎችን ባካተተ መልኩ የተዉጣጣ ነበር። የዚህን ግብረ ኃይል የድርጊት መርሀ ግብር አፈጻጸም የሚከታተለዉ በረከት ስምዖን ሲሆን፤ የግምገማዉን ሪፖርት ለመረጃና ደህንነት ዋና ዳይሬክተሩ ጌታቸዉ አሰፋ ያቀርባል።
በዚህ ተዋረዳዊ አሰራር መሰረት የግብረ ኃይሉ አባላት ዋነኛ ስራ በሚሰሩበት መስሪያ ቤትና በመኖሪያ አካባቢያቸዉ የስለላ ስራዎችን በመስራት የደህንነት ስጋት የሚታይባቸዉን አካባቢዎችና ግለሰቦች በመለየት ለኮማንድ ፖስቱ ጥቆማ ያሰጣሉ። ግልባጩንም በሳምንቱ መጨረሻ በግብረ ኃይሉ ጠርናፊ አማካይነት ለበረከት ስምዖን ይላካል። ይህ ግብረ ኃይል ከህዳር ወር የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ የጥምቀት በዓል አከባበርን በተመለከተ በከተማዉ የሚናፈሱ ወሬዎችን በመለቃቀም አደራጅቶ ሪፖርት ያቀርባል። በዓሉ እንዳይከበር “እንቅፋት” ይሆናሉ የሚሏቸዉን ተሰሚነት ያለቸዉን የከተማዋን ወጣቶች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እየተከታተሉ ለኮማንድ ፖስቱ ይጠቁማሉ። ከሁሉ በላይ የሚገርመዉ የዚህ ግብረ ኃይል ክንፍ የሆነዉ የቤተ ክህነት የስለላ መስመሩን የሚመራዉ ቡድን ሲሆን፤ አባላቱ በአርባ አራቱም አብያተ ክርስቲያናት ያሉትን የኃይማኖት አባቶችን፣ ቀሳዉስትን፣ ዲያቆናትንና የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችን ከምኩራብ አስከ ደጀ ሰላም ድረስ ያለዉን እንቅስቃሴቸዉን እየተከታተተሉ ይሰልላሉ፤ “ጸረ-ጥምቀት በዓል” (ጥምቀት አይከበር የሚል) አመለካከት የሚታይባቸዉን የቤተክርስቲያን ሰዎች ለኮማንድ ፖስቱ አሳልፈዉ ይሰጣሉ። በጎንደር ዩኒቨርስቲ፣ በመምህራን ኮሌጅ፣ በቴክኒክና ሙያ፤ በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ የመንግስትና የግል ደርጅቶች ዉስጥ ከሚማሩና ከሚሰሩ ተማሪዎችና ሰራተኞች ዉስጥም ተመሳሳይ ዝንባሌ (ጸረ-ጥምቀት) የሚታይባቸዉ በዓሉ ከመድረሱ በፊት እንዲታሰሩ ተደርጓል። በአሁኑ ሰዓት ሁለተኛ ዙር “የተሃድሶ ፕሮግራም” ተሳታፊ እንዲሆኑ በሚል በብርሸለቆ ዉስጥ ታጉረዉ ከሚገኙ የጎንደር ወጣቶች (ካህናትን ጨምሮ) ብዙዎቹ በዚህ ግብረ ኃይል ጠቋሚነት የታፈሱ ናቸዉ።
የግብረኃይሉ ጫና ውጤትና “ቱሪስቶች”
በቃሉ የሚጸናዉ ብዙሃኑ ጎንደሬ ጥምቀት ላይ ላለመታደም የተማማለ ቢሆንም በበረከት ስምዖን አደራጅነት የሚመራዉ ግብረ ኃይል ድራማዊ ድባብ ያለዉ ቀዝቃዛ የጥምቀት በዓል እንዲከበር “የአንበሳዉን ድርሻ” ይዟል። በአንድ ለ አምስት ከተደራጁት ዉስጥ በዓሉ የሚመለከታቸዉ የኦርቶዶክስ ክርስትና አማኞች ከከተራዉ አስከ ሚካኤል ንግስ ዕለት ለሦስት ተከታታይ ቀናት በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ተደርጓል። ከአንድ ለ አምስት አደረጃጀት በተጨማሪ የሊግና የፎረም አባላት፣ የልዩ ልዩ ማኅበራት አመራሮችና የጥቅም ተጋሪዎቻቸዉ፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲና በመምህራን ኮሌጅ የነጻ ትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸዉ በመማር ላይ ያሉ የሥርዓቱ አገልጋዮች፣ የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ሰራተኞች፣ በማኅበር የተደራጁ “የጎንደር ከተማ አዝማሪዎች ማህበር” አባላት፣ በጎንደር ዙሪያ የሚገኙ የገጠር ቀበሌ አመራሮች፣ የገጠር ቀበሌ የካቢኔ አባላት ለበዓል አሟቂነት በልዩ እንክብካቤ ከከተራዉ ጀምሮ እንዲገኙ ተደርጓል። የገጠር ቀበሌ አመራሮች፣ ተከታይ ጀሌዎቻቸዉ እንዲሁም አበል ተከፋይ አዝማሪዎች ለባህላዊ ጭፈራ አሟቂነት ጥቅም ሲሰጡ ተስተዉሏል።
ዉንብድና የማያልቅበት የገዥዉ መደብ ስብስብ ከወቅቱ የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ በጎንደር የጥምቀት በዓል የዉጭ አገር ቱሪስቶች ቁጥር ወደ ዜሮ ፐርሰንት ዝቅ እንደሚል ቀደም ብሎ የተረዳ በመሆኑ የተለመደ የማጭበርበር ሥራዉን ሰርቷል። በጎንደርና አካባቢዉ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነ ለማስመሰል፤ “ቱሪስት” በሚል ጎንደር ላይ እንዲገኙ የተደረጉት የዉጭ አገር ዜጎች በአብዛኛዉ በአገሪቱ ዉስጥ ያለ ከልካይና አለም አቀፍ ጨረታ ሳይወጣ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ግልጽነት በጎደለዉ መልኩ እንዲሰሩ እድሉ የተሰጣቸዉ የቻይናዉ ሲ.አር.ሲ (CRC) እና የጣሊያኑ ሳሊኒ (SALINI CONSTRUCTION – የህዳሴዉን ግድብ የሚሰራዉ) ደርጅት ተጠቃሽ ናቸዉ። በእነዚህ ድርጅቶች ዉስጥ የሚሰሩ አንድ መቶ ሃያ የዉጭ አገር ዜጎች ከየፕሮጀክት ሳይቶች ተሰባስበዉ በ“ቱሪስት” ስም ከተማዋ ላይ እንዲገኙ ተደርጓል። ወጪያቸዉን የሸፈነዉ ደግሞ የታደሰ ጥንቅሹ መጫዎቻ የሆነዉ የብአዴኑ “ጥረት” ነዉ። ይህ ምስጢር ያልገባቸዉ በደንበኛ ድርቅ ተመተዉ የከረሙት የጎንደር ትልልቅ ሆቴሎች እንግዶቹ የአገልግሎት ክፍያዉን በዶላር እንዲፈጽሙ ቢማጸኑም ሰሚ አላገኙምና ሆቴሎቹ “ይህንስ ማን አየብን” በሚል ሀበሻ በሚስተናገድበት የአገልግሎት ክፍያ በጉዞ ወኪል (ኤጀንት) በኩል ክፍያቸዉ ተፈጽሟል። የጉዞ ወኪሉ የብአዴኑን “ጥረት” የስፖንሰር ወጪ ለመቀነስ በአየር ላይ የተፈጠረ የበረከት ስምዖን ምናባዊ ድርጅት ነዉ።
ቆርጦ ቀጥሉ “የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን” በዜና እወጃ ሰዓቱ መልሶ መላልሶ ጥምቀትን ከተመለከቱ የዜና ፋይል ክምችት ጋር እያቀናበረ “የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ የክልሉና የፌዴራል ባለስልጣናትና የከተማዉ ነዋሪዎች  በተገኙበት በድምቀት ተከበረ … በበዓሉ የተገኙ የዉጭ አገር ቱሪስቶችም በበዓል አከባበሩ ደስተኛ መሆናቸዉን ገለጹ…” በሚል ለቀዘውቃዛዉ ጥምቀት ሞቅ ያለ ዜና ሰራለት።
ቀዝቃዛዉ ጥምቀት እንዲህ ባለ ዜና ተከሽኖ ቀረበ … እዚህ ደርሰናል!! ዉሸት በአይነት!! ፕሮፖጋንዳ በገፍ!! ሽንፍላ ይመስል ታጥቦ የማይጸዳዉ የገዥዉ መደብ ስብስብ ጥልቅ መበስበሱን ግፋ በለዉ ማለቱን ቀጥሏል …ግን እስከ መቼ ይዋሻል?! የዉሸት እድገት በፕሮፖጋንዳ መልኩ መጠመቃችን ላይበቃ ጥምቀቱንም እንዲሁ?! ድንቄም መታደስ … እኛስ ታዘብን ጥልቅ መበስበስ!!
ቴዎድሮስ ኃይሉ
(ይህ ዘገባ ከፎቶው ጋር በተለይ ለጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ የተላከ ነው፤ ፎቶው ጥምቀት 2009ዓም በጎንደር ከተማ “በተከበረበት” ወቅት)

No comments:

Post a Comment