Translate

Tuesday, October 4, 2016

“አሁን ደም ተቃብተናል፤ ዕርቅ የለም፤ ሌላ ሳይከተል ልቀቁልን”፤ “ከህወሃት ጋር ድርድርና እርቅ ብሎ ነገር የለም” የሕዝብ ምላሽ ሃይለማርያም ውረድ ተባለ!


irreecha79
ኦሮሚያ ብቻ ሳትሆን ድፍን አገርን ማቅ ያለበሰው የጅምላ ጭፍጨፋ እያደር አጥንት የሚያደቅ መረጃ እየወጣበት ነው። ህወሃት የእርቅ መንገዶችን በሙሉ አሟጦ የቀበረበት ይህ “ይቅርታ የሌለው ወንጀል” እስካሁን የ678 ንጹሃንን ህይወት አጥፍቷል። የትዳር ጓደኛውን አስከሬን በግል ተሽከርካሪ ጭኖ እያነባ ወደ ቤተሰቡ የወሰደ አለ። ገንዘብ ተዋጥቶለት የሚስቱን አስከሬን ጭኖ ወደ ሱሉልታ የተጓዘ መኖሩ ተሰምቷል። እናትና ልጅ ባንድነት ቀብራቸው ተከናውኗል። በአንድ ቀን ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ወገኖች ከቤተሰባቸው ጎድለዋል። አስከሬን አሁን ድረስ እየተቆፈረ እየወጣ ነው። ሃይቅ ላይ የተንሳፈፉ አስከሬኖች እየተለቀሙ ነው። ህዝብ ቁጣው ገንፍሎ በተለያዩ ስፍራዎች እምቢተኛነቱን እየገለጸ ነው። ህወሃት ግን አሁንም ይዋሻል።

በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች ስፍራውን ለቅቀው እንዲወጡ በታጣቂዎች እስከታዘዙበት ድረስ የታዘቡትን ለቪኦኤ ሲያስረዱ ሁሉም ነገር ሰላማዊ ነበር። ህዝብ ተቃውሞውን ሲገልጽ የነበረው በሰላማዊ መንገድ ነበር። ምንም ዓይነት ትጥቅ ያልያዙ የኦሮሚያ ፖሊሶች ከህዝቡ ጋር በኦሮሚኛ እየተነጋገሩና ህዝብም “የእኛ” ሲላቸው ይደመጥ ነበር። ታዲያ ሰላማዊ ተቃውሞ ከነበረ ለምን በአየር፣ በታንክና፣ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ተፈጸመ? የሚለው ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኗል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሕዝብ ላይ ጦር ሠራዊቱ ጭፍጨፋ እንዲፈጽም ትዕዛዝ የሰጠው ሃይለማርያም ደሳለኝ በህወሃት ቴሌቪዥን ቀርቦ “እስካሁን ባለኝ መረጃ 52 የሚጠጉ ሞተዋል” በማለት ጸቡን ያስነሱትን ህግ ፊት እንደሚያቀርብ ዝቷል። ምንም ዓይነት የጥይት ድምጽ ሳይሰማ ህዝብን በመጠበቅ ከፍተኛ ትጋት ላሳዩት የጦር ሠራዊት አባላት ብሎ ለጠራቸው የአጋዚ ታጣቂዎች ምስጋናውን አሰምቷል። ሃይለማርያም በትዕዛዝ እርቅ በጠየቅ ባጭር ጊዜ ውስጥ ህዝብ ላይ ክተት መታውጁን አብሳሪ ሆኖ “አማራ ክልል” ሰላማዊ ዜጎች እያስጨረሰ ነው። አሁን ደግሞ የህወሃት አንጋቾች ለፈጸሙት የጅምላ ጭፍጨፋ እውቀና መስጠቱ ከሃዘኑ በላይ ህዝብን ያቆሰለ ጉዳይ ሆኖ እያነጋገረ ነው።irreecha75
እልቂቱ በደረሰበት ዕለት ዜና ያነበበችው የቪኦኤዋ አዳነች ፍስሃዬ “በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ” ያለቻቸው፣ “የአማጺ ባንዲራ በመያዝ ነጻነት እንፈልጋለን የሚሉ ነበሩ” ስትል አወላግዳና አሳንሳ ያቀረበችው የተንሸዋረረ መረጃ የሃይለማርያምን ያህል ባይሆንም ትዝብት ውስጥ የሚጥል እንደሆነ አስተያየት የሰጡ አሉ። ወዲያው አዳነች ይህን ብላ ስትጨርስ የተቀበላት ሌላው የቪኦኤ ባልደረባ የኦሮሚያ ክልልን ጠቅሶ እስከ 4 ሚሊዮን ህዝብ በበዓሉ ላይ ተሳታፊ እንደሚሆን አመልክቶ ነበር።
ከዚህ አስዛኝና ዘግናኝ ዜና በኋላ በሟቾችና በቆሰሉ ዜጎች አኻዝ ዙሪያ ለተፈጠረው ሰፊ ክፍተት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ “ህወሃት በቁጥር ማምታታቱ የተለመደ ነው። አይገርምም። የሚደንቀኝ የዓለም ሚዲያዎች እነሱን አምነው የሚዘግቡት ነው” ሲሉ ህወሃት ቀጣፊ እንደሆነ የታሪክ ሪኮርዱ እንደሚመሰክርበት ያመለክታሉ። ምርጫ ሲባል 100 ከ100፣ ኢኮኖሚ ሲባል የድርብ አሃዝ ዕድገት … በማለት የሚጠቀሱት አቶ ኦባንግ “ህወሃት ከግድያ ውጪ ችግርን የሚፈታበት እውቀት የሌለው፣ እምነቱም፣ ፍጥረቱም፣ ዕድገቱም፣ ዕቅዱም ንጹሃንን መግደል ብቻ ነው። የሚጠቅመው ሲሆን ድሮ እንደሚያደርገው ነጻ አወጣችኋለሁ የሚለውን የራሱንም ሰዎች ያጠፋል” ሲሉ ጊዜው የተራራቁ አካላት ተሰባስበው አንድ አካል የሚሆኑበት ጉዳይ ላይ ቅድሚያ የሚሰጥበት እንደሆነ አመልክተዋል። አያይዘውም “ቀደም ብለን አካል ሆነን ቢሆን ኖሮ እየነጣጠሉ አይገሉንም ነበር። ምክንያቱም አካል አንዱ ክፍል ሲጎዳበት ሁለመናውን ያመዋልና” ብለዋል፡፡ በቀናነትና ህዝብን ባስቀደመ መልኩ አንድ አካል መሆን፣ ከዘር ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ መስጠት፣ እንደ ጎሣ ሳይሆን እንደ ሰብዓዊ ፍጡር፣ እንደ ኢትዮጵያዊ ማሰብና መሰባሰብ፣ መታገል ግድ መሆኑን አስመረውበታል።
irreecha77ሃይለማርያም “ጥቂት ጸረ ሰላም ሃይሎች” ሲል አሳዳሪዎቹን ለማስደሰት እንዲህ ባለው መሪር ሃዘን ቢሳለቅም የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ እንዳለውና ኦፌኮ ለቪኦኤ እንዳረጋገጠው በኦሮሚያ ህዝባዊ እምቢተኛነቱ ተፋፈሞ ቀጥሏል። በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች የአገዛዙ መዋቀሮች ላይ ጉዳት ደርሷል። በምዕራብ ሃረርጌ የህወሃት ንብረት የሆኑ የሰላም አውቶቡሶች ወድመዋል። በወለጋ፣ በምስራቅ ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በጅማ፣ በጉጂ፣ አርሲና በሌሎችም ስፍራዎች ህዝብ በህወሃት ንብረቶች ላይ የበቀል ርምጃ ተወስዷል። የአምቦ ውሃና የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ስራ አቁመዋል። እንደ ዜናው የህዝባዊ እምቢተኛነቱ አራማጆች “ቀጣዩ እርምጃ ሕዝብን እያስገደሉና እየገደሉ ያሉትን ግለሰቦችን ያጠቃልላል” ማለታቸውን ይፋ አድርጓል።
ህዝባዊ እምቢተኛነቱ እየከረረ እንደሚሄድ የሚጠበቅ ሲሆን በዛሬው እለት (ሰኞ) በአምቦ 4 ንጹሃን፣ በቢሾፍቱ 2 በአጋዚ ሠራዊት መገደላቸውን የአይን ምስከሮች ለጎልጉል ተናግረዋል። ህዝብ ሃዘኑ ሳያጠግለት ዛሬም ነፍስ ማጥፋት ላይ የተጠመደው ህወሃት ላለፉት 25 ዓመታት የፈጸመውና ያደረሰው በደል አንድ ላይ ተዳምሮ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሊስማማ የሚችልበት አማራጭ ሁሉ መዘጋቱን ብዙዎች እየተናገሩ ነው።
የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ከህወሃት የቀረበላቸውን የእርቅ ጥያቄ አንቀበልም ማለታቸው የዚሁ የቆየው ሰቆቃ ውጤት ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ። ለዚህም ይመስላል ህወሃት በገሃድ እየገደለ በጓሮ የለመነው እርቅ የተዘጋበት። በቤተ እምነት ሰዎች በኩል የእርቅ ጥያቄ የቀረበላቸው እኒህ ሁለት ግንድ ህዝቦች ህወሃት ላለፉት 25 ዓመታት እርቅንና ፍቅርን እንደገደለ አመልክተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህወሃት ያደረገውንና እያደረገ ያለውን፣ በተለይም በኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ የፈጸመውን “አረመኔነት የተሞላበት፣ የታቀደና ዝግጅት የተደረገበት” የተባለውን የጅምላ ጭፍጨፋ የተመለከቱ “ህወሃት/ኢህአዴግ ራሱን ለመጨረሻ ጊዜ ገደለ። ምን አልባትም የመጨረሻ እድሉ የሆነውን የባለአደራ መንግስት የማቋቋም ተስፋ የማግኘት ዕድሉም ሊኖረው አይችልም” ሲሉ እየተደመጡ ነው።irreecha78
የኦሮሞ ህዝብ የኢሬቻን በዓል ሲያከናውን ከተፈጸመበት የጅምላ ጭፍጨፋ በፊት ህወሃት በሃይለማርያም ደሳለኝ አማካይነት የተለያዩ ቤተ እምነት ሰዎችን ስለ ዕርቅ ተማጽኖ ነበር። በሃይለማርያም የጥሪ ደብዳቤ መነሻ በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ የየእምነቱ የወንጌል አገልጋዮች አዲስ አበባ ተገኝተው ነበር። እነዚሁ ሰዎች ኦሮሚያና አማራ ክልል በመሄድ ህወሃትን ከህዝብ ጋር እንዲያስታርቁ  ተጠይቀዋል። በጥያቄው መሰረት እያንገራገሩ የእምነት አባቶቹ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው በመሄድ አግባብ ያላቸውንና ለሕዝብ ቅርብ ከሆኑት ጋር ተወያይተው ተመልሰዋል። ምላሻቸውንም ይዘው ሃይለማርያም ቢሮ በመገኘት ህዝብ የሰጠውን ምላሽ አስረድተዋል። የጎልጉል የአውሮፓ ዘጋቢ በስብሰባው “ተገኝቻለሁ” ካሉ ያገኘውን መረጃ ጠቀሶ እንዳለው የሰዎቹ ምላሽ ሃይለማርያምን አስደንግጦ ነበር።
“በመጀመሪያ በትህትናና በህግ እንዲሁም በልመና ለረዥም ጊዜ ጥያቄ አቅርበናል። ዕርቅ ጠይቀን አልተቀበሉንም። አሁን ደም ተቃብተናል። ሰዎች ሞተዋል። ሌላ ሳይከተል ይልቀቁን ነው የሚሉት” ሲሉ የአማራዎችን አቋም አንደኛው መልዕከተኛ አቀረቡ። “ከህወሃት ጋር ድርድርና እርቅ ብሎ ነገር የለም” ሲሉ ጠቀለል አድርገው ኦሮሞዎች የመለሱት መልስ ምን እንደሆነ ሌላኛው መልዕክተኛ አስረዱ። ይህ በጓሮ ሲደረግ ህወሃት የሚመራው ሚዲያና የህወሃት መሳሪያ የሆኑ ክፍሎች የነጻነት ጥያቄ የሚያቀርቡትን የኅብረተሰብ ክፍሎች አሸባሪ፣ የጥፋት ኃይሎች፣ ተላላኪዎች፣ ጸረ ልማቶች፣ አተራማሾች … ወዘተ እያለ እያወገዙ ነበር፤ አሁንም ነው።
ገና ከጅምሩ ሃይለማርያም “ህዝብ ይሰማችኋልና ዕርቅ አውርዱልን” ብሎ ሲጠይቅ አንድ ትውልዳቸው ከኦሮሞ የሆነ አንጋፋ የወንጌል ሰባኪ “እግዚአብሔር ይህ ‹አገዛዝ› እንደሚወድቅ የተናገረው ከ10 ዓመት በፊት ነው። ልጄ ለምን እዚህ ውስጥ ገባህ? እጅህን አንሳ፣ ውጣ፣ መንግስት ከአንተ እጅ አይደለችም፣ የብዙ ሰዎች ደም በእጅህ አለ። ይህ ቦታህ አይደልም። ልቀቅ…” ብለው ማሳሰቢያ እንደሰጡ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው የመረጃ ሰው በመናገር የሃይለማርያምን ምላሽ ሳያብራሩ አልፈውታል። ዘጋቢው ማብራሪያ ቢጠይቅም “ቢሰማ ኖሮ ኢሬቻ ሲያከብሩ በነበሩ ወገኖች ላይ አንድም የጥይት ድምጽ አልተሰማም” ብሎ አያወራም ነበር ሲሉ የመጠየፍ ስሜት እየተሰማቸው ተናግረዋል።
ላለፉት እጅግ በርካታ ዓመታት ስለ ዕርቅ መላ ሲቀርብ ሞት እንደ ቡሽ ክዳን ያስፈነጠረው መለስ እያሾፈ ይህ የባልና ሚስት ጠብ አይደለም በማለት ብዙ ሲቀለድ ኖሯል፡፡ በ97ቱ ምርጫ ወቅት ይኸው መለስ ከሰማይ በታች በማንኛውም ጉዳይ ላይ እደራደራለሁ በማለት የሕዝብን ቁጣ እንዲበርድ ካደረገ በኋላ የድርድሩን ምላሽ የተቃዋሚ መሪዎችን ወኅኒ በመወርወር ንቀቱን አሳይቷል፡፡ ከዚያም በተደጋጋሚ የቀረቡ የብዙዎች የዕርቅ ጥያቄዎች የፈሪ ልመና ተደርገው የተወሰዱባቸው ጊዜያት ጥቂት አይደሉም፡፡
ህወሃት/ኢህአዴግ ከዚህ በኋላ የሚያቀርበውም ሆነ የሚቀርብለት የዕርቅ ጥያቄ እንደሌለ በርካታዎች የሚስማሙበት ሃቅ እየሆነ መጥቷል፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ የወላድ መሃን አለመሆኗ እንደገና የሚታይበት ወቅት ላይ መሆኑ አገር ወዳድ የሆኑና በሕዝብ ዘንድ ታማኝነት የሚጣልባቸው አገርን የማዳን ሥራ የሚሠሩበትና ከተደበቁበት የሚወጡበት ጊዜ ነው፡፡ ጥቃቱ እስከ መቅኔያችን የተሰማን በሙሉ በተለያዩ መጠሪያዎች ሳንከፋፈል በኅብረት የተቃውሞ ድምጽ የምናሰማበት ጊዜ ነው የሚለው አስተሳሰብ የበርካታዎች እየሆነ መጥቷል፡፡ (መግቢያ ፎቶ: Reuters, ሌሎቹ ከማኅበራዊ ገጾች የተገኙ)

No comments:

Post a Comment