ይገረም አለሙ
ስለ ቀድሞው ጠቅላይ ምስትር መለስ ዜናዊም ሆነ በአንድ ቅኝት ሲያዘፍኑዋቸው ስለነበሩ ፓርቲዎች እንዲሁም ከተከታይነት ያለፈ ምንም ፋይዳ ስላልነበራቸው ሹማምንት ብዙ የተባለ ቢሆንም ዛሬም አድናቂ ነን ባዮች እወደድ ባዮች በመንግሥታችሁ አትርሱን ባዮች ወዘተ ታላቁ ባለ ራዕዩ ወዘተ ከማለት አልፈው አቶ መለስ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ሲሰሩና ሲባትሉ እንደሞቱ ሊነግሩን ይዳዳቸዋል፡፡
አቶ መለስ ሀገር ከማስገንጠል ህዝብ እሰከ መነጣጠል (ያውም እንደ አሰቡት አልሆነላቸውም) ወደብ አልባ ከማድረግ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት እስከ መጣር የደረሱ ለዛሬው ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድም ነቀርሳ የሆኑ እኩይ ድርጊቶቻቸው እንኩዋን ኢትዮጵያዊ አለም ያወቃቸው ናቸው፡፡ጥቅም ማስተዋልን ነስቶአቸው ዛሬ ስለ አቶ መለስ ተቃራኒውን የሚነግሩን ሰዎች አንድ ቀን የአቶ መለስ ትሩፋት ሲደርሳቸው ከእኛ ብሰውና ልቀው ሲኮንኗቸው እንሰማ ይሆናል፡፡
እኔ ዛሬ በትንሹ ማንሳት የምፈልገው አቶ መለስ የሞቱት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ሲለፉና ሲደክሙ ሳይሆን ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ሲማስኑ እንደሆነና ራሳቸውን የገደሉት ራሳቸው መሆናቸውን ነው፡፡
ለወራት ተደብቆ የቆየው ህልፈታቸው ከተገለጸ በኋላ ታላቁ እና ባለ ራዕዩ መሪ በሚሉ ቅጽሎች እየታጀቡ ከየድርጅቶቹ የተሰጡ መግለጫዎችም ሆኑ በየባለሥልጣኖቹ የተነገሩ ህዝቡ ሲላቸው ከነበረው በላይ የአቶ መለስን ጠቅላይ ገዥነት ያረጋገጡ ናቸው፡፡እንደተነገረን ከሆነ ከደደቢት እስከ ምልክ ቤተ መንግሥትም ሆነ በሀያ አንድ አመቱ የመንግሥትነት ዘመን የተፈጸመው ሁሉ የአቶ መለስ የብልህ አእምሮ ውጤት ነው፡፡ይህ በመታመኑም ነው ከእኛ የሆነ ምንም የለም የርሳቸውን ሌጋሲ እናስቀጥላለን እንጂ ተብሎ ሀገር በሙት መንፈስ የምትመራው እነርሱም በሙት መንፈስ ቅዠት የሚተራመሱት፡፡
አቶ መለስ በፓርቲ ስራ በሊቀመንበርነት ሳይወሰኑ በበታች ካድሬዎች የሚሰሩ ስራዎችን ሳይቀር ሰርተዋል፡በመንግሥት ሥልጣናቸው በጠቅላይ ምኒስትርነት ደረጃቸውና ድርሻቸው ሳይወሰኑ የምኒስትሮችን የመምሪያ ኃላፊዎችን የኤክስፐርቶችን ወዘተ ስራ ሰርተዋል፡፡ከዚህ ሁሉ አልፈውና ወርደው በርዕዮተ ዓለማዊ ብቃቱ፣ በድርጅታዊ ታማኝነቱና በጽሁፍ ችሎታው ኃላፊነት የሚሰጠው አንድ ሰው ጠፍቶ የድርጅት ልሳን ዋና አዘጋጅ እንደነበሩም ተነግሮናል፡፡ እውነትም “ጠቅላይ” ግን አንደምን ችለውት ኖሩ? መቼም አቶ መለስ ይህን ሁሉ ሰብስበው መያዛቸው አንድም ችሎታውና ብቃቱ ስላላቸው ሁለትም በብቃት የሚሰራ ሰው በመታጣቱ ነው ብሎ የሚሞግት ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡
ከርሳቸው ጠቅላይነት ባልተናነሰ የሚገርመው የሌላው ሎሌነት ነው፡፡ደግሞ ይህንኑ ሎሌነታቸውን በአደባባይ እየወጡ መናገራቸው፡፡ ሁሉም ነገሮች የአቶ መለስ ሀሳቦች፣እቅዶች፣ራዕዮች፣ ክንውኖች፣ ወዘተ ከሆኑ ሌላው በየደረጃው የነበረው የሥልጣን ካባ ደርቦ ክብርት ክቡር ሲባባል የኖረው ሁሉ ምን ሲሰራ ነበር፡፡ የአቶ መለስን እቅድ ከመመሪያ ጋር ወደ ታች እየላኩ ማስፈጸም ይቻል ስለነበር ፓርላማውም ምኒስትሮች ምክር ቤትም ሹማምንቱም አያስፈልጉም ነበር፡፡
ኢትጵያውያን በእውቀታቸው በሙያና ልምዳቸው ሀገራቸውን እንዳይጠቅሙ በማድረግ ብቻ ሳይወሰን በዙሪያቸው የተሰባሰቡት ባለሥልጣናትም በህግ ተገድቦ በአወጅ ጸድቆ የተሠጣቸውን ኃላፊነት እንኳን እንዳይወጡ ቀየዶ የያዘው የአቶ መለስ ጠቅላይ ገዥነት ሀገርንና ህዝብን ጎድቷል፣ለውድቀት ዳርጓል፡፡ በህውኃት ቅርጫት ውስጥ አስገብተው የቆለፉባቸውን ድርጅቶችም፣ራሳቸውንና ቤተሰባቸውንም ጎድቷል፡፡
አቶ መለስ በህውኃት ውስጥ በስራም ይሁን በሴራ ሁሉን በልጠውና ጥለው በብቸኝነት ተቆጣጥረውት ኖረዋል፡፡ ኢህአዴግ በሚል ጭንብል ውስጥ በተሰባሰቡ አራት ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙትም ሰዎች ራሳቸውን አሳንሰው ርሳቸውን አተልቀው እንዲያዩና የርሳቸውን መሪነት ሰጥ ለጥ ብለው ያለምንም ጉርምርምታ አንዲቀበሉ አድርገዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ሥልጣኑን ለራሳቸው አመቻችው ንግግራቸው የማይተች፤ ስራቸው የማይነቀፍ፤ ሲሳደቡ የሚጨበጨብላቸው፤ ተረት ሲያወሩ የሚሳቅላቸው፤ያዘዙት ሁሉ የሚፈጸምላቸው መሾም መሻር ማሰር ማባረር ያልተጻፈ ሥልጣናቸው ሆኖ ሞት ባይቀድማቸው ኖሮ ፓርቲየ እስከፈለገኝ በሚል ማስመሰያ መቼም ከምኒልክ ቤተ መንግሥት አይወጡም ነበር፡፡
ነገር ግን በትግሉ ወቅት ሁሉን ጥለው በመንግሥትነቱ ከሁሉ በልጠው የወጡበትን ዘዴም መንገድም ያውቁታልና ሁሉን ተቆጣጥረው በዙሪቸያው ባሉ ሰዎች ምትክ የለሽ መሪ እስከመባል ቢበቁም በርሳቸው መንገድ ተጠቅሞ ወደ ርሳቸው ወንበር ለመምጣት የሚያስብ ፈጽሞ አይኖርም ብለው ተረጋግተው መኖር ግን አልቻሉም፡፡ ሌባ እናት ልጇን አታምንም አይደል የሚባለው፡፡
የያዝከው መሳሪያ መዶሻ ብቻ ከሆነ የምታየው ሁሉ ምስማር ይመስልሀል እንደሚባለው አቶ መለስ ለሥልጣን የበቁትና የዕድሜ ልክ ጠቅላይ ምኒስትር ለመሆን የቻሉት በሸፍጥና በሴራ ስለሆነ ቀና ብሎ የሚራመድና ሰው ሆኖ ለመኖር የሚሞክር ሲያዩ በርሳቸው መንገድ ወደ ርሳቸው ሥልጣን ለመምጣት የሚያስብ እየመሰላቸው መንገድ መዝጋት ካልሆነም ፈጥኖ ገለል ማድረግ በዚህ የሚቆም ካልመሰላቸው ስም ማጥፋት መወንጀል ማሰር ሲብስም ማስወገድ ዋና ስራቸው ሆኖ ነው የኖሩት፡፡
ለሌሎቹ ባዶ ወንበር ሰጥቶ ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት ሥልጣን ማንነታቸውን የሚያሳዩበት መድረክ በመንፈግ በርሳቸውና በሌሎቹ መካከል ያለውን ርቀት ከቀን ወደ ቀን እያሰፉ ለሀገር መሪነት ቀርቶ ለፓርቲ መሪነት፤ ለአማራጭነት ቀርቶ ለተተኪነት እምነት የሚጣልበትና ተስፋ የሚደረግበት ሰው እንዳይኖር አድርገዋል፡፡ ባልጠበቁት መንገድ ብቅ ያለ ከታየም ቶሎ መልክ በማስያዝ ወደ ርሳቸው ወንበር ሊያደርስ የሚችለውን መንገድ እንዳያውቅ አውቆም ከሆነ መሞከር አይደለም እንዳያስበው ማድረግ መለስን እረፍት የለሽ አድርጎ ለሞት ያበቃቸው ስራቸው እንደነበረ ቀድመን ከገመትነውና ከአወቅነው በላይ ከሞታቸው በኋላ የተነገረን ያረጋገጠው ሀቅ ነው፡፡
“ተከታዮች የመከተል ብቻ ሳይሆን የመሪነት አቅጣጫን የማስተካከልም ድርሻ እንዳላቸው ቢታወቅም ” በአቶ መለስ የሥልጣን ዘመን በተግባር የታየውና ከሞታቸው በኋላም በባለሥልጣኖቹ የተረጋገጠው ሀቅ በፓርቲም በመንግሥትም ውስጥ በየደረጃው ያሉ ባለሥልጣኖች በአቶ መለስ መልካም ፈቃድ ተሾመው የርሳቸው ተከታይ ከመሆን የዘለሉ እንዳልነበሩ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ተከታዮች ደግሞ መሪው በንግግርም ይሁን በተግባር ቢሳሳት የማያርሙ፣ተፈጻሚነቱ ጉዳት የሚያስከትል ነገር ቢያቅድ ማሻሻያ የማያቀርቡ፣ህግ ሲጥስ ተው የማይሉ፣ስልጣኑ ድንበር ሲያጣ የማይገድቡ ወዘተ በመሆናቸው ውድቀቱን አለያም ሞቱን የሚያፋጥኑ ነው የሚሆኑት፡፡
በርግጥ እንደ አቶ መለስ ያለ ወንበሩን ለአንድ ቀን እንኳን የማያምን ፈሪ አንባገነን አቤት ወዴት ብሎ የሚታዘዘውን እንጂ ለምን አንዴት ብሎ የሚጠይቀውን እንደማይፈልግ ይታወቃል፤ በመሆኑም መጀመሪያ በደንብ ተጠንቶ ይመለመላል፣ ከዛም በአቶ በመለስ ጸበል ተጠምቆ ይሾማል፤ይህን ሁሉ ካለፈ በኋላ እኔ ሰው ነኝ ማለት የሚቃጣው ከሆነ የአቶ መለስ መላ ይጠብቀዋል፤ በየግዜው የታየው ሹም ሽርም ሆነ ከቦታ ቦታ ማዘዋወር ሁሉም በብቃት ማነስ የተፈጸመ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ሰው በዚህ ቦታ ከዚህ በላይ ከቆየ ወደ ሥልጣን የሚወስደውን “ስራም ሴራም” ሊካን መንገዱንም ሊያውቅ ይችላል ከሚል ስጋት አንገት ለማስደፋትና ወኔ ለመስለብ የተደረገ ነው፡፡ለዚህ ደግሞ ተተኪው በምንም መመዘኛ ከተነሳው የማይበልጥ መሆኑን ማየት ብቻ በቂ ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡
በልጅ እያሱ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ነጋድራስ ኃይለጊዮርጊስ ወልደሚካኤል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩትን በጅሮንድ ተክለሀዋርያትን ከከንቲባነት ያሰናበቱበትን ምንያት ሲናገሩ “እኔ የምፈልገው ራሴ ስዘጋው የሚዘጋና ስከፍተው የሚከፈት ሳጥን አንጂ አንደ ተክለሀዋሪያት በራሱ ኃይል የሚከፈትና የሚዘጋ አይደለም ”ማለታቸው ተጽፎ ይገኛል፡፡አቶ መለስም አይናገሩት እንጂ ይህን ነው ሲያደርጉ የኖሩት፡
አቶ መለስ ነጋድራስ ያሉዋቸውን አይነት ሰዎች መፈለጋቸውና በዙሪያቸው ማሰባሰባቸው ለሥልጣናቸው ነው፡፡ ርሳቸው እንደፈለጉ የሚዘጉት የሚከፍቱት ሳጥን ሆነው ለመኖር የፈቀዱት ሰዎች ግን በርግጥ ያሳዝናሉ፤ ዜጋ በመሆናቸውም ያሳፍራሉ፡፡ እንደዚህ ስብዕናቸውን አዋርደውና በሞራል ኮስሰው የሚኖሩ ሰዎች መሪውን ሰማየ ሰማያት ሰቅለው ያለሆነውን ብቻ አይደል ወደ ፊትም ሊሆን የማይችለውን ነህ እያሉ ምድር ላይ ያለውን እውነት እንዳያይ፤ የሚገዛትን ሀገር ምንነትና አንዴትነት እንዳይረዳ፤ የህዝብን ተቃውሞ የምሁራንን አስተያየትና ምክር እንዳይሰማ፤ ከእኔ በቀር ብሎ እንዲታበይና ከህዝብ ርቆ፣ ተነጥሎ ተጠልቶ እንዲኖር ስለሚያደርጉት ውርደቱን፣ውድቀቱን ሲበዛም ሞቱን የሚያፋጥኑ ናቸው፡፡
አቶ መለስ ዋናው ጉዳያቸው ለሥልጣናቸው ያላቸው ስስት ሆኖ የርሳቸውን ጠቅላይ ገዢነትና ለዚህ ያበቃቸውን የህውኃት የበላይነት ለማስጠበቅ እንቅልፍ አጥተው ሲሰሩም ሲያሴሩም ኖሩ፡፡ ተው ብሎ የሚመክራቸው፣ እንዲህ ቢሆን ብሎ አስተያየት የሚሰታጣቸው ይህ መሆን የለበትም ብሎ የሚከራከራቸው የሥልጣን ገደብህንና የሥራ ድርሻህን እወቅ የሚላቸው እረፍት አድርግ ብሎ ሹክ የሚላቸው ወዘተ አንድ ሰው አጠገባቸው ሳያስደርሱ ጨሥልጣን ወይንም ሞት ብለው ሲማስኑ ጤናቸው ተቃወሰ፡፡
መታመማቸውን አንዳወቁ ግዜ ወስደው በወቅቱ ህክምና ቢከታተሉ ሊድኑ ካልሆነም ትንሽ ዕድሜ ሊጨምሩ ሲችሉ እንዲህ ጥለውት ሊሄዱ ወንበራቸውን አላምን ብለው በቁማቸው ሲንገታገቱ ህመማቸው ጸንቶ ከህክምናውም ጥበብ ከሀኪሞቹም እውቀትና አቅም በላይ ሆነና “ታሞ አይድኔ” ሆኑ፡፡ ተኝተው ሳይነሱ ሆስፒታል ገብተው ሳይመለሱ ሀያ አንድ አመታት ለአንድም ቀን ያልተለዩትን ወንበር ለዘለአለም ጥለውት ሄዱ፡፡ በግዜ ከሥልጣን ተሰናበተው እረፍት አግኝተው ብዙ ሊሰሩ ብዙ ሊጽፉ ሲችሉ፤ ከሥልጣን ወርዶ በሀገሩ ለመኖር የበቃ የመጀመሪያው መሪ ተብለው በታሪክ ሊዘከሩ በትውልድ ሊከበሩም ሲችሉ የሥልጣን ነገር ሆኖ ራሳቸውን ራሳቸው በአጭሩ ቀጩት፡፡
ይህ ሁሉ ልፋት ድካማቸው ለሀገር በማሰብ ለሕዝብ በመቆርቆር ቢሆን ኖሮ ፈጣሪም በዚህ እድሜአቸው አይጨክንባቸውም ነበር፡፡ በየግዜው ከእኩይ ተግባራቸው አንዲታቀቡ ከጥፋት መንገድ አንዲመለሱ ምልክት ሰጥቶአቸዋል፡(የህውኃትን መሰንጠቅ የሻዕቢያን ወረራ የ 97ትን ምርጫ መጥቀስ ይቻላል) የሥልጣን ነገር እያዩ ማስተዋልን እየሰሙ ማዳመጥን ስለሚነሳ አጋጣሚዎችን መጠቀም ያልቻሉት መለስ ሥልጣን ወይንም ሞት ብለው በክፋት መንገዳቸው ቀጥለው ራሳቸውን ገደሉ፡፡
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች፤ፈጣሪዋም ይሰማታል፣ አንዲህም ይገላግላታል፡፡ሁሉን እንደፈቃዱ በግዜው የሚሰራው ፈጣሪ በኢትዮጵያ ላይ የሚነሱትን ሁሉ ግዜውን እየጠበቀ ያነሳቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን አትንኩ፡፡
No comments:
Post a Comment