Translate

Thursday, July 16, 2015

ፍርድ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ወሰነ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በእነ ዘመነ ካሴ መዝገብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ድረስ ለተጠቀሱት ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ወሰነ፡፡ የፌደራል አቃቤ ህግ ‹‹ከአንዳርጋቸው ጋር በአካል ተገናኝታችኋል›› የሚል ክስ የመሰረተባቸው ተከሳሾቹ ‹‹ከአንዳርጋቸው ጋር ተገናኝታችኋል ከተባለ አቶ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ታስረው የሚገኙ በመሆናቸው መከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ይታዘዝልን›› የሚል ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡Ato Andargachew Tsige, Ginbot 7
የፌደራል አቃቤ ህግ በበኩሉ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በእነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ እና በእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መዝገብ ላይ ክስ ቀርቦባቸው በእድሜ ልክና በሞት እንዲቀጡ ተወስኖባቸው የህዝባዊ መብታቸው የተሻረ በመሆኑ በምስክርነት ሊቀርቡ አይችሉም ብሎ ተቃውሟል፡፡ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ህዝባዊ መብት በመሻሩ ለፍርድ ስራ ልዩ አዋቂ ወይንም ነባሪ ሆነው መስራት አይችሉም ያለው የፌደራል አቃቤ ህግ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በተጨማሪ ምስክርነት ቀርበው መመስከር አይገባቸውም ሲል የተከሳሾቹ ጥያቄ ውድቅ እንዲሆን ለፍርድ ቤቱ አመልክቶ ነበር፡፡

ሆኖም ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ አቶ አንዳርጋቸው እንዲቀርቡላቸው የጠየቁት ለዋስት አሊያም ልዩ አዋቂ ምስክር ሆነው ሳይሆን ነበሩበት የተባለውን ጉዳይ ለመናገር ለምስክርነት በመሆኑ፣ ምስክርነትም ግዴታ እንጅ መብት በመሆኑ ሰኞ ሰኔ 13/2007 ዓ.ም በእነ ዘመነ ካሴ መዝገብ ለተከሰሱት ተከሳሾች ልደታ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲመሰክሩ ወስኗል፡፡ ተከሳሾቹ አቶ አንዳርጋቸው የት እንደሚገኙና ማዘዢያው የት ተብሎ ሊፃፍላቸው እንደሚገባ ተጠይቀው ለቃሊቲ ማረሚያ ወይንም ለፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ሊጻፍላቸው እንደሚገባ፣ ካልቀረቡላቸውም ክሳቸው ከአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር የተገናኘ በመሆኑ አቶ አንዳርጋቸው በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ አቤቱታ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡
ተከሳሾቹ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡላቸው በጠየቁበት ወቅት በዳኞችና በአቃቤ ህጎች ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ መፈጠሩንና ከአቶ አንዳርጋቸው ይልቅ ሌሎች መከላከያ ምስክሮችን ማቅረብ እንደሚችሉ፣ አቶ አንዳርጋቸውን በመከላከያ ምስክርነት ለማቅረብ መሞከር እንደሌለባቸው እንደገለፁላቸው ታውቋል፡፡ ዳኛው በድንጋጤ ‹‹እኛ እዚህ ጉዳይ ላይ የለንበትም›› ማለታቸውን ተከሳሾቹ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውስጥ ላነጋገራቸው የነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር ገልጸውለታል፡፡

No comments:

Post a Comment