በዲ/ን ተረፈ ወርቁ
የኢሕአዴግ መንግሥት አሸባሪዎች ናቸው፣ በዜጎች ክቡር ደም የቆመውን ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ የተደራጁ ናቸው፣ በውጭ አገር ካሉ ሰላማችን፣ ዕድገታችን በቅናት ብግን እያደረጋቸው ካሉና አገራችንን ለማተራመስ ቆርጠው ከተነሡ ከፈረደበት ሻቢያ፣ ሽብርተኛ ድርጅቶችና ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር አብረው ይሠራሉ፣ የአገርንና የሕዝብን ደኅንነትና ፀጥታ አደጋ ላይ ጥለዋል፣ በኢትዮጵያ ሰላምና በሕዝቦቿ ልዑላዊነትም ላይ በመደራደር ይቅር የማይባል ክህደት ፈጽመዋል ያላቸውን የዞን ፱ ጦማርያንና ሌሎች ጋዜጠኞችን ከአንድ ዓመት በላይ ፍርድ ቤት ሲያመላልሳቸው ቆይቷል፡፡
ማብቂያ የሌለው በሚመስል ቀጠሮ በነጋ ጠባ ወደ ፍርድ ቤት ሲመላለሱ የቆዩ ወገኖቻችንም ያን አምኖ ለመቀበል ቀርቶ ለመስማት እንኳን የሚከብድ ክስና የወንጀል ማስረጃ አቅርቤባችኋለኹ ያላቸውንና ፍርዳቸውን ከእውነት፣ ከፍትሕ አምላክ ሲጠብቁ የነበሩ ወገኖቻችንን መንግሥት በነጻ ተሰናብታችኋል ሲል የመለቀቃቸውን ዜና እንደ ዋዛ አበሰረን፡፡ መንግሥት እነዚህን ወገኖቻችንን በነጻ ያሰናበተበትን ምክንያቱን አልነገረንም፡፡ ቅሉ እንዲነግረንም የምንጠብቀው ሰዎችም ያለን አይመስለኝም፡፡
ኢሕአዴግ እንደቀደመው ጊዜም መንግሥት መሐሪ ነውና በአገርና በሕዝብ ላይ ላደረሳችሁት ክህደትና ወንጀል ይቅርታ ጠይቁና ነጻ ውጡ የሚለውን የተለመደች ብልጣብልጥነቱንም አልተጠቀመም፡፡ በዚህ ሰበብም ሽማግሌዎችንም እነዚህን ሰዎች እባካችሁ ማልዱኝ፣ አማልዱኝ በሚል አላደከመም፡፡ እንደው ብቻ ደርሶ ነጻ እኮ ናችሁ ሲል በአንድ ሺ አንድ መረጃና ሰነድ ወንጀላቸውን፣ ኃጢአታቸውን ሰማይ የሰቀለውን እነዚህን ሰዎች በአንዲት ማዘዣ ቃል ብቻ ነጻ ናችሁ ሲል አሰናበታቸው፡፡
መቼም ዘንድሮ ኢሕአዴግ እፍረትና ይሉኝታ ይሉትን ባህላችንን አሸቀንጥሮ የጣለ ነው የሚመስለው፡፡ ምርጫውን መቶ በመቶ አሸንፌያለኹ ብሎ ባወጀ መሬት አንቀጥቅጥ ድሉ ማግሥት ደግሞ እነዚህን በአገር ልዑላዊነት በሕዝብ ጥቅም ላይ የተደራደሩ ሰዎችን ማን ወንድ ነው ፍርዳቸውን ሳያገኙ፣ የእጃቸውን ሳይከፈሉ ከእጄ የሚያወጣቸው ሲል እንዳልነበር፣ እንዳልተገዘተ ኹላ ‹‹ሾላ በድፍኑ›› እንዲሉ አበው ከአንድ ዓመት በላይ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን እነዚህን ወገኖች በነጻ አሰናብቼቸዋለኹ እንግዲህ ደስ ይበላችሁ ሲል ዜናውን፣ የምስራቹን አበሰረን፡፡
እኛም መንግሥትን እንደው እነዚህን ወገኖች ስታስርም ሆነ ስትፈታ ምክንያትህ ምንድን ነበር በሚል ጥያቄ ራሳችንን ስናሞኝ አንገኝም፡፡ መንግሥት ምክንያቱ ምንም ይሁን ምንም እነዚህ ወገኖቻችን በነጻ በመለቀቃቸው የሁላችንም ደስታ፣ ሐሤትና እረፍት ነው፡፡ ሌሎችም ያለ ፍርድ የታሰሩ፣ ፍትሕን የተነፈጉ ወገኖቻችንም ነጻ ይወጡ ዘንድም ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ ግማሽ ደስታ ባሻገር ግን አሁንም ሌላ ጥያቄ፣ ሌላ ብሶት፣ ሌላ ቁጭት አሁንም በብዙዎች ልብ ውስጥ ተከድኖ አለ፡፡
‹‹በፍርድ ከኼደች በቅሎዬ፣ ያለ ፍርድ የኼደች ቆሎዬ›› እንዲሉ አበው እንዲህ በእናት ኢትዮጵያ ምድር ስለተረገጠው እውነት፣ ስለዘመመው ፍትሕ፣ ስለተዛነፈው ፍርድ የብዙዎች ቁጭት፣ ብሶትና ምሬት ከትናንትና ይልቅ ዛሬ ተባብሶ ይቀጥላል፡፡ እናም መንግሥት ሆይ ‹‹የፍትሕ ያለ፣ የእውነት ያለኽ፣ የፍርድ ያለኽ!›› የሚለው የሕዝብ፣ የኢትዮጵያ እናቶች እንባና ጩኸት ሰማይን እንዳናወጠ፣ ምድሪቱን እንዳጨቀየ ወደ ሰማይ መፍሰሱን ቀጥሏል፡፡ ግና መንግሥት አሁንም ድረስ በዚሁ ኹሉ በሕዝብ ብሶት፣ እዬዬና እሮሮ ውስጥ የሚሰማ ጆሮን፣ የሚያይ ዓይንን የታደለ አይመስልም፡፡
ግና የራሄሎች እንባ ወደ ጸባኦት አምላክ ጆሮ በደረሰ ጊዜ፣ ያ የፍርድ ጽዋ የሞላ ጊዜ ግን… ወየው ፍርድን ለሚያጣምሙ፣ ፍትሕን ለሚያዛቡ የእውነት ጠላቶች!! እነዚህ ልባቸውን እንደ ግብጻዊው ፈርኦን ልብ ፈጽመው ያደነደኑ፣ በኢትዮጵያ አምላክ ላይ ልባቸውን ያኮሩ፣ በሕዝባቸው ላይ የጭቆናን ቀንበር ያጠበቁ፣ ፍርድንና ፍትሕን ያዛቡ፣ መበለቲቱንና ባልቴቶችን ያስለቀሱ፣ የሽማግሌዎችንም ፊት ያላፈሩ ዓመፀኞች፣ የአምላክን ወሰን የሌለውን ትዕግሥቱንና ምሕረቱን እንደ ከንቱ ነገር የቆጠሩና ያጣጣሉ አምባገነኖች ኹሉ ራሳቸውን ለመቅሠፍት፣ ለውርደት ሞት የጠበቁ፣ አጥፊው የሞት መልአክ በቤታቸው ደጃፍ አድብቶ፣ ቆሞ ያለ መሆኑን ያውቁት ዘንድ በእርግጥም የግድ ይላቸዋል፡፡
ከትናንትና መሰሎቻቸው አሳዛኝ የውርደት ታሪክና የአምላክ እውነተኛ ፍርድና ፍትሕ ለመማር እምቢ ያሉ ኹሉ የውርድት፣ የጥፋት ታሪክን በራሳቸው ላይ ለመድገም ዛሬም በተጠንቀቅ ላይ እንዳሉ እየታዘብን ነው፡፡ ግና ቢሆንልንና ቢሰምርልን ምኞታችን፣ ጸሎታችን ግን አበው እንደሚመርቁት፡- ‹‹ዕድሜ ለንስሓ ዘመን ለፍሥሐ!›› እንዲሰጣቸው፣ እንዲያድላቸው ነው፣ ጥፋታቸውንና ክፋታቸው፣ ዓመፃቸውና በደላቸው ሌላውም እንዳይተርፍ ሲባል፡፡
ታላቁ መጽሐፍ፡- ‹‹እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት፣ ለባልቴቶች ዳኛ ነው፡፡ እግዚአብሔር እስረኞችን በኃይሉ ያወጣቸዋል፡፡›› እንዲል በግፍ ስለተጋዙባቸው፣ ፍትሕ ስለተነፈጋቸው፣ ፍርድ ስለተጓደለባቸው ልጆቻቸው ወደ ሰማይ የተረጨ የኢትዮጵያውያን ምሰኪን እናቶች እንባ እንዴት በከንቱ ይቀራል?! እርጅና ባደከመው ጉልበታቸው፣ ችግርና ጉስቁልና ከሰው መልክ ባወጣቸው እናቶች የተጎሳቆለ ፊት ላይ የፈሰሰው ያ እንባ፣ በልጆቻቸው ናፍቆትና ስስት ነፍሳቸው ዝላና ደክማ በነጋ ጠባ የቃሊትንና የቅሊንጦን ወኅኒ ቤቶች እንደ መቅደስ ሲሳለሙ የነበሩ የእነዚህ እናቶች ድካምና ልፋት፣ ሰቀቀንና ናፍቆት በአምላክ ፊት በእውነትም ይዘከራል፣ ይታሰባል፡፡
መቼም ለሚያስተዳድረው ሕዝብ የሚገባውን ፍቅርንና ክብርን ለመስጠት ዳገትን የመውጣት ያህል ለከበደው መንግሥታችን ይህን ደግመን ደጋግመን እንላለን፡፡ ፍቅር በሌለበት እውነት የለም፤ እውነትም በሌለበት ፍትሕ የለም፣ ፍትሕ በሌለበትም ምሕረት ተብሎ ነገርም አይታሰብም፡፡ እናም ገና በምድሪቱ ላይ ፍቅር እስክትነግሥ፣ ፍትሕ እንደ ወንዝ ውኃ ሞልቶ እስኪፈስ፣ ፍርድ ድል ነሥቶ እስኪወጣ፣ እውነት እስኪያሸንፍ፣ ዓመፀኞችና በደለኞች የእጃቸውን እስኪያገኙ ድረስ የምድራችን ግፉአን ጩኸት፣ እንባና ደም የፍርድ ያለኽ ማስተጋባቱን አያቆምም፡፡
ስለፍቅር፣ ስለእውነት፣ ስለፍትሕ የእናት ኢትዮጵያ ለቅሶና እንባዋ አሁንም በጉንጮቿ ላይ ነው፡፡ መጽሐፍ እንደሚልም፡- ‹‹የሰማይ አምላክ ስለችግረኞች ጩኸት አሁን እነሣለሁ፣ እገለጣለኹ፣ ፍርድንም አደርጋለኹ!›› እንዲል ኢትዮጵያ የአምላኳን ቅን ፍርድ፣ እውነተኛ ፍትሕ በምድሯ እስኪገለጥ ድረስ ዛሬም እጇን ዘርግታ በትዕግሥት፣ በጽናት ትጠብቃለች!! ‹‹ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሐ ሀበ እግዚአብሔር!›› እንዲል መዝሙረኛው ዳዊት፡፡
No comments:
Post a Comment