አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በወያኔ ከሰነዓ አለም አቀፍ አውሮፓላን ጣቢያ ታፍነው ከተወሰዱ በዛሬው ዕለት ሰኔ 16 ቀን 2007 ዓ. ም፣ አንድ ዓመት ይሞላቸዋል። የወያኔ አረመኔዎች ይህን ዓይነት የውንብድና ተግባር ሲፈጽሙ በከፍተኛ ደረጃ ያሰሉት፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በማፈን፣ ንቅናቄው ብሎም ሕዝቡ፣ ለዕኩልነት፣ ለፍትህና ለነጻነት፣ የሚያደርገውን ትግል ለማዳከምና ከተቻለም ደግሞ ለማጥፋት እንደሆነ፣ ምንም የማያጠራጥር ጉዳይ ነው።
ለመሆኑ የወያኔዎች ስሌት በምን ያህል ትክክል ነበር ?
ለመሆኑ የወያኔዎች ስሌት በምን ያህል ትክክል ነበር ?
ባለፈው አንድ አመት ውስጥ፣ ወያኔ በአቶ አንዳርጋቸው ላይ የፈጸመው የውንብድና አፈና ተግባር፣ ንቅናቄያችን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በሐገር ውስጥም ሆነ በውጭ ባለው ሕዝብ ልብ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ሌላው ቀርቶ ከአፈናው በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ንቅናቄያችንን በጥርጣሬ የሚመለከቱ ወገኖች በአደባባይ ወጥተው፣ ” እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ” በማለት አቶ አንዳርጋቸውና ንቅናቄው ለሚታገሉለት ሕዝባዊና ሐገራዊ ዓላማ መቆማቸውን በግልጽ አሳይተዋል። እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በሐገር ውስጥ፣ በምድር ላይና በውጭ ሐገር የሚገኘውን የንቅናቄያችንን አካላት ተቀላቅለዋል። ቀደም ሲል በንቅናቄያችን በተለያዩ ደረጃዎች ይሰሩ የነበሩ ዓባላቶች ከአፈናው በኋላ ለትግሉ ያላቸውን ቁርጠኝነት በከፍተኛ ደረጃ ጨምረዋል።
የአቶ አንዳርጋቸውን አፈና ተከትሎ፣ የንቅናቄው አመራር መሰረታዊ የትግል እንቅስቃሴዎቹን በስፋትና በጥልቀት በመፈተሽ አስፈላጊውን ማሻሻያዎችና ማስተካካያዎችን አድርጓል። ንቅናቄያችን አቶ አንዳርጋቸው ለረጅም ጊዜ የደከሙለትን ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ የመታገለን ጥረት አሳክቶ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዓርበኞች ግንባር ጋር ሙሉ ለሙሉ ተዋህዷል። ከዚህም በተጨማሪ የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን ጨምሮ፣ ከሌሎች አምስት በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋራ በጥምረት ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሷል።
በሌላ በኩል ያለፈው አንድ አመት የወያኔ የዘረኛ ዓምባገነን ቡድን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በሕዝብ ላይ የሚፈጽመውን የአፈና፣ የግድያ፣ የዕስርና የድብደባ ውንብድና ተግባር አጠናክሮ የቀጠለበት ዓመት ነበር ። ለዚህም ጸረ ሕዝብ ተግባሩ፣ በባህርዳር ከተማ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ያደረሰውን ግድያ፣ በሰላም እንታገላለን ብለው ይንቀሳቀሱ የነበሩትን የአንድነትና የመኢሀድ ድርጅቶች ማፍረስ ብቻ ሳይሆን፣ ዓባሎቻቸው ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ የድብደባና የዕስር ወንጀል መጥቀስ ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ በኦሮምያ፤ በአፋር፤ በጋምቤላ፤ በኦጋዴን፤ በትግራይና በደቡብ ክልሎች ይህ ነው የማይባል አፈና፤ ግድያና የሕዝብ መፈናቀል በሰፊው አከናውኗል:: ከምርጫው ጋር ተያይዞም በአደረበት ስጋት የተነሳ በርካታ፣ በተለይ ወጣቶች ላይ፣ የመደብደብ፣የማዋከብ የዕስርና የግድያ ተግባር የፈጸመው በዚሁ አቶ አንዳርጋቸውን ከአፈነበት ቀን ጀምሮ በተቆጠረው የአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ነበር። በጣም የሚገርመው ለራሱ አመቻችቶ ያዘጋጅውን ምርጫ እንኳን ሙሉ በሙሉ አሸነፍኩ ብሎ ከአወጀም በኋላም፣ ከምርጫው በፊት በሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ወንጀል አጠናክሮ መቀጠሉ ያለበትን የስጋትና ጭንቀት ደረጃ የሚያሳይ መረጃ ነው ።
የወያኔ በራስ የመተማመን ደረጃ ከመቼውም ወቅት ይልቅ እጅግ አሽቆልቁሎ የታየውም ባለፈው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ነበር። በሐገር ውስጥ ይነሳብኛል ብሎ በሚያስበው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ስጋት ምክንያት ይህን ስጋት ለመቀነስ በአንድ መንገድም ይሁን በሌላ ይረዱኛል ብሎ ያሰባቸውን በአካባቢው የራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት ያላቸውን ቀደም ሲል ወቀሳ ቢጤ እንደመሰንዘርም ዕልህም እንደመጋባትም ይዳዳቸው የነበሩትን መንግስታት ባለሥልጣኖች በመማጸንና ሐገር ውስጥ በመጋበዝ ማንነቱን አበጥሮ ለሚያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአደባባይ ወጥተው ወያኔ ያልሆነውን ነው ብለው ምስክርነት እንዲሰጡለት ማድረጉ የወያኔ ስጋት የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ የሚያሳይ ሌላው መረጃ ነው።
በዚህ አጋጣሚ ንቅናቄያችን አቶ አንዳርጋቸውን አፍነው ለወያኔ የሸጡትን የየመን ባለሥልጣኖች ድርጊት በሚመለከት በጊዜው በሰጠው መግለጫ ላይ በግልጽ እንዳስቀመጠው፣ “ጊዚያዊ ጥቅምን በማየት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዕኩልነት፣ ለፍትህና ለነጻነት የሚያደርገውን ትግል ከወያኔ ጋር በቀጥታም ሆን በተዘዋዋሪ በመተባበር ለማፋን መሞከር፣ ታሪካዊ ስህተት መስራት ነው!” እንዳለው ሁሉ፣ ዛሬም የሌሎች መንግስታት ባለ ሥልጣኖች እንደ ትላንትናዎቹ የየመን ባለሥልጣኖች ጊዚያዊ ጥቅምን ብቻ በማየት ሌላ ታሪካዊ ስህተት እንዳይደግሙ ከወዲሁ ለማሳሰብ ይወዳል።
በንቅናቂያችን እምነት ከዚህ በላይ በጥቂቱም ቢሆን ለማሳየት እንደተሞከረው ያለፈው አንድ ዓመት ያሉት መረጃዎች በሙሉ የሚያሳዩት ወያኔ አቶ አንዳርጋቸውን በማፈን ለማዳከም ያሰበው ትግል ይበልጥ ተጠናክሮና ተቀጣጥሎ በርካታ አንዳርጋቸውዎችን ከማፍራቱም በላይ ብዙዎች ለነጻነታቸው መተኪያ የሌላትን ህይወታቸውን እስከመስጠት የሚያደርስ ዕልህ ውስጥ ገብተዋል። ወያኔ እንዳሰበውና እንዳሰላው ትግሉ መዳከም ሳይሆን መሬት እያያዘና እየተጠናከረ በመምጣቱ የወያኔ ስጋት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ እየጨመረ ሄዷል። ይህም ሁኔታ የዛሬ አንድ ዓመት በፊት ወያኔ አቶ አንዳርጋቸውን ሲያፍን ያሰላው ስሌት እጅጉኑ የተሳሳተ እንደነበረ በግልጽ አረጋግጧል። የወያኔ የአፈና ተስፋ ገና በአፈናው ማግስት እንደ ጧዋት ጤዛ ተኗል። ከአለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በመላው ሀገሪቷ ተጠናክሮ የምናያቸው የወያኔ የጭካኔ እርምጃዎች የሚያመለክቱት ይህንኑ ስጋትና ጭንቀት ነው። የወያኔ የቅዥትና የስጋት የዛፍ ላይ እንቅልፍ፣ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ተሸጋግሮና ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ንቅናቄያችን፣ አርበኞች ግንቦት 7፣ ለዕኩልነት ለፍትህና ነጻነት የሚደረግ ትግል፣ በተለይ እንደወያኔ ባለ ዘረኛ አምባገነን ቡድን በበላይነት በሚዘወር ሐገራዊ ሁኔታ ውስጥ፣ ምን ያህል ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን አስቀድሞ ጠንቅቆ ያውቃል። ይህም ሆኖ ግን ባለፈው አንድ ዓመት፣ የትግል ጓዳችን የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው በወያኔ እጅ ከወደቁበት ጊዜ ጀምሮ እየደረሰባቸው ያለውን መከራና ስቃይ እንዲሁም ይህ ሁኔታ በቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ ያስጀመረውን የጭንቀት ዘመን፣ ለአንድ ሴኮንድም ቢሆን መዘንጋት አይችልም።
ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 በአቶ አንዳርጋቸው ላይ በአፈናው የተነሳ የደረሰው መከራና ስቃይ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ ለፍትህ ለዕኩልነትና ለነጻነት በመቆማቸው በወያኔ አረመኔዎች ቁም ስቅላቸውን የሚያዩት በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ሰቆቃ የሚያበቃው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ በሚያደርገው ሁለ ገብ ትግል በመሆኑ ማንኛችንም በአቶ አንዳርጋቸውም ሆነ በሌሎች ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እንደራሳችን ጥቃት አድርገን የሚሰማን ወገኖች በሙሉ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከታፈኑበት አንድ አመት ወዲህ የተጀመረውን ተስፋ የሚሰጥ እንቅስቃሴ አጠናክረን ወደ ውጤት ደረጃ በማድረስ መጭው ዘመን የሕዝብ የፍትህ የእኩልነትና የነጻነት ተስፋ የሚለመልምበት ፣ የወያኔ አምባገነን ሥርዓት እድሜ የሚያጥርበት ዘመን እንዲሆን የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ንቅናቄያን ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል።
ክብር ለፍትህ ለእኩልነትና ነጻነት መስዋትዕነት ለከፈሉና እየከፈሉ ላሉ ታጋዮች!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
አርበኞች ግንቦት7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ
ሰኔ 16 ቀን 2007 ዓ.ም.
ሰኔ 16 ቀን 2007 ዓ.ም.
No comments:
Post a Comment