ዛሬ ለምን እነደሁ እንጃ፤ ረዳት አብራሪ ሃይለመድን አበራ በማለዳው በአዕምሮዬ ተመላለሰ። ምን ደርሶ ይሆን… ምን ተብሎ ይሆን… ኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመስራት የሰው ሃገር እስራትን ያስመረጠውን በደል የሚነግርን መቼ ይሆን… ወይስ ያቺ እህቱ እና እኒያ ወንድሙ እነዳሉት የስዊዝ ሃኪሞችም ህመምተኛ ነው ብለው ወደ ህክምና ልከውት ይሆን… (ከሆነም ካለሆነም ኢትዮጵያችን ውስጥ ጤነኛው ማነው… መቼስ ነው የምንድነው…) እያልኩ የባጥ የቆጡን ሳንሰላስል ቆየሁና፤ ድንገት የስዊዘረላንድ ወጪ ጉዳይ ሚኒስቴርን ድረ ገጽ ጎግልን ጠየኩት።
የተባረክ ጎግል “ካንተማ አልድብቅህም ደንበኝ!” ብሎ ሰጠኝ። ከድረ ገጹ ላይ የኢሜል አድራሻቸውን ለቅም አደርኩና “Dear Sir Madam…” ብዬ ሳበቃ (እኔ ከእናነት ሃሳብ እና ናፍቆት በስተቀር ደህና ነኝ) የሚለውለውን ሳላካትት የወንድማችን ሃይለመድን አበራን ነገር ከምን አደረሳችሁት… አሁን በምን ሁኔታ ላይ እነዳለ ለማወቅ ፈለጌ ነው ይህንን የኢሜል መልዕክት ወደ እናንተ መስደዴ ስል በትህትና ጠየኳቸው።
የስዊዘርላንድ ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤትም እግዜር ያክብረው እና በቃል አቀባዩ ጄኒት ባለመር በኩል ባደረሰኝ ኢሜል፤ ጉዳዩን የያዘው (እኛ “ጠቅላይ ፍርድ ቤት” እንደምንለው አይነት) እነደነርሱ ደግሞ Attorney General of Switzerland (OAG) በሚሉት የህግ መስሪያ ቤት ቢሆንም ለመረጃ ያክል ግን ሰለሁኔታው በጀረመንኛ እና በፈረሳይኛ የተሰጠ መገለጫ እንካ… ብሎ ልኮልኛል።
እኔም ጀርመንኛዬን እና ፈረሳይኛዪን ይዤ ጎግልን የቅድሙ ሰውዬ ነኝ ድጋሚ መጣሁ እባክህ ይሄንን ተርጉምልኝ… አልኩት፤ ጎግልም “ጣጣ የለውም” ብሎ ወደ እንግሊዘኛ መለሰለኝ፤
እና እንግሊዘኛው እንደሚለው፤ “ረዳት አብራሪው ሃይለመድን አበራ አሁን በህግ ቁጥጥር ስር ሆኖ ምርመራ እየተደረገበት ነው። ያለበትን ቦታ ለመጥቀስ ወይም ሌሎች መረጃዎችን ለማቀበል፤ አሁን ምርመራው የደርሰበት እና ያልደረሰበት ደረጃ አይፈቅድም፤ ምርመራው ገና ያልተጠናቀቀ በመሆኑ ሌሎች ዝርዝር መረጃዎችንም መስጠት ለቀጣይ ሂደት እንቅፋት ሊሆን ይችላለ ተብሎ ይገመታልና መናገር ያስቸግረናል። በጥቅሉ የኢትዮጵያዊው ረዳት አበራሪ ጉዳይ ዛሬም በምርመራ ላይ ነው።” ሲል ያትትና “የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ግን ሰኞ ባረፈ በሶስተኛ ቀኑ ረቡዕ በፈረነጆቹ አቆጣጠር በ19/02/14 ሊሄድ ወዳሰበበት ቦታ (እርሱም ጣሊያን ነው) ተሸኝቷል።” ይላል።
የስዊዘርላንድን ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሀገራቸው የስራ ቋንቋዎች በፈረንሳይኛ Merci beaucoup እንዲሁም በጀርመንኛ Vielen Dank በማለት አመሰግናለቸዋለሁ!!!
ለወንድማችን ሃይለመድን አበራም መለካሙን መመኘቴ አይቀርም።
No comments:
Post a Comment