የማለዳ ወግ
ነቢዩ ሲራክ
ሰሞኑን ጠቃሚ መረጃ የምንለዋወጥባቸው ማህበራዊ ገጾቻችን በሙግት ንትርክ ማዕበል ተውጠው ተመለከትኩ … ከእምየ ምኒሊክ እሰከ በደሌ ቢራ ፣ ከድንቁ ትንታግ ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ መግለጫ ፣ እርማት እስከተሰጠበት እንቁ መጽሔት ፣ ከታሪክ አዋቂው የሃገር ሽማግሌ ፕሮፊሰር ይስሐቅ የታሪክ ቀደምት ትንታኔ ታሪክ እስከ ማይጠቅመን የጁሃር መሃመድ ዘመቻ ሁሉም ሰሞነኛ ዝብሪት በየአይነቱ ሰማን ። ይህ ሁሉ ታዲያ በፈረንጆች አመት በዋዜማው ባይሆን ደስ ባለኝ! ይህም የእኛ ነገር ፣ የእኛ ኑሮ ነውና ምን ያደርጉታል?
ባለሁበት የሳውዲ ምድር በአለም እንደ ጨው የተበተንን የዚያች ሃገር ዜጎችን ትኩረት ሳቢ ብቻም ሳይሆን አስጨናቂ ቀንን ተፋጦ ማወጫ ያጣ ወገን ጩኸት ደምቆ እንዳይሰማ የእኛ ነገር አልተመቸውም ! ሌላው ቀርቶ ጥቂት “ያገባናል” ያልን መረጃን በቀላሉ እየተለዋወጥን በምንገኝባቸው ማህበራዊ ገጾች ከአንድ የአለም ጫፍ ወደ ሌላው የአለም ጫፍ በብርሃን ፍጥነት የሚሰራጨው የጥላቻ ፖለቲካ የመረጃ ቅብብል መተንፈሻ ፣ ጉዳታችን ለአለም መንገሪያ ሜዳችን እንዳያጨልምብን ሰጋሁ ! ከሁሉም የሚያሳዝነው የምንወዳቸውና የምናከብራቸው የተማሩ የተመራመሩት ወገኖቻችን ሳይቀሩ በዝብሪቱ አዙሪት ተጠልፈው መግባታቸውን እየታዘብን ነው ።