Translate

Tuesday, September 4, 2012

አዎን መለስ ዜናዊ ገና አልሞተም


ከእንቁጣጣሽ በፊት ወደ ሥራው ይመለሳል” ብለው መዋሸታቸውን አውቀናል። እውነቱን ከህዝቡ መሠወር የእነ በረከት ስምዖን ባህል ነው። አማራ ሳይሆን አማራን እወክላለው ብሎ በአማራ ህዝብ አናት ላይ የተቀመጠው በረከት ስምዖን መዋሸት ሙያው ነው።በረከትን የመሰሉ እና በውሸት ሙያ የታወቁ ግለሰቦች ተሰባስበው ውሸትን የድርጅታቸው ባህል አድርገውታል። በባህላቸው መሠረት እውነቱን ከህዝቡ ሊሰውሩ ቢሞክሩም በግድ እውነቱ ተገልጦ መለስ ዜናዊ በጠና ታሞ ሰንብቶ ማለፉን በግዳቸው አውጀዋል። መለስ ዜናዊ ቢሞትም የሰውየው አምላኪዎች “መለስ አልሞተም” እያሉ ነው።ራእዩም ህልሙም ከእኛ ጋር ህያው ሆኖ አለም እያሉ ነው። ከአምላኪዎቹ  መካከል ስንቶቹ የመለስ ዜናዊን ራእይ ለይተው ያውቁት እንደሆነ አናውቅም።
እኛም አዎን መለስ ዜናዊ ገና አላለፈም ህያው ሁኖ በህይወት አለ እንላለን። ራእዩም ህልሙም ቅዥቱም በአገራችን ላይ ተንሰራፍቶና ህይወት ዘርቶ እስካለ ድረስ የሞተም የተለወጠም ነገር የለም። መለስ ዜናዊ የዘረጋውን የዘረኝነት፤ ኢ-ፍትሃዊ አስተዳደር እና ጭካኔን አጠናክረው ለመቀጠል እጃቸውን ወደ ደሙ ወጪት የሰደዱ፤ የደሙንም ጽዋ አብረው የተጎነጩ ዘረኞች በመንበሩ ላይ እስካሉ ድረስ የመለስ ማለፍ የሚለውጠው ነገር የለም።
እግዜርም ሰውም የሚጸየፋቸው የደም እጆች፤ የሃሰት አንደበቶች፤ ደንዳና ልቦች፤ ነውረኛ ተክለሰውነቶች በመንበሩ ላይ እስካሉ ድረስ አዎን መለስ እና ህልሙ በህይወት አሉ።
የመለስ ዜናዊ ራእይ በትግራይ ሥም የራሱን ገዥ ጉጅሌ አዘመኖና የእነርሱንም የበላይነት ገንብቶ ማየት ነው። ገዥ ጉጅሌዎቹም እኛ ብቻ ወርቅ፤ እኛ ብቻ ጀግና ብለው ራሳቸውን ሰይመው በአገሪቷ ጫንቃ ላይ ከነ ድንቁርናቸው ተንጠላጥለዋል። እነዚህ ጥቂቶች ብዙሃኑን ተጭነው፤ ብዙሃኑም እነርሱን ተሸክሞ እንዲኖር ያላቸውን ቅዥት እንደያዙ ዛሬም በመንበሩ ላይ አሉ። የእነዚህ ቡድኖች የበቀል፤ የጥላቻ እና የንቀት ሰይፍ ወደ ሰገባው አልተመለሰም።የመዘዙትን የበቀል ሰይፍ ተማምነው፤ ሰውን ሁሉ ንቀው፤ ራሳቸውን ሁሉን አዋቂ፤ ሁሉን አድራጊ አድረገው የቆጠሩ ቡድኖች አሁንም  ሁሉን ለማድረግ ሁሉን ለመግዛት መክረውና ተማምለው ከመጋረጃው ጀርባ ተሰልፈዋል። ከመጋረጃው ጀርባ ሰባት ግለሰቦች ራሳቸውን የአገሪቷ መሪዎች እኛ ነን ብለዋል። ከሰባቱ አራቱ በአገራችን ላይ ብዙ በደል፤ ብዙ ወንጀል የፈጸመው የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት መሪዎች ናቸው። ይሄ የንቀታቸውን፤ የመንደርተኝነታቸ እና የማን አለብኝነታቸው ጥሩ ማሳያ ነው። ይህ ነፍሰ ገዳይ ቡድን ዛሬም መለስ ዜናዊ የተከለውን ዘረኝነት፤ ዝሪፊያና፤ ኢ-ፍትሃዊነትን ለመቀጠል ምሎ ተገዝቷል።
እነዚህ ራሳቸውን ለይተው ወርቅ እና ጀግና ብለው የሰየሙ ግብዞች ከደምና አጥንት ቆጠራ ተላቀው በአገሪቷ ውስጥ ፍትሃዊ ሥርዓትን ለመገንባት የሚያስችል ስብእና ያላቸው አይደሉም። በብሄራዊ ደረጃ ለማሰብም ገና ከከንቁላሏ እንዳልተፈለፈች ጫጩት ስለሆኑ ወደ ዚያ ትልቅ አስተሳሰብ መድረስ የሚችሉም አይደሉም። ህወሃት ውስጥም ከመንደሩ ዘልቆ ወጥቶ ለማሰብ የሚችል ተክለ ሰውነት ያለው ግለሰብ አይገኝም። መሪያቸው መንደረተኛ አስተሳሰቡን እንደያዘ ትቶላቸው የሄደው ያው መንደርተኝነትንና “እኔ ብቻ” ባይነትን እንጂ ብሄራዊ አስተሳሰብንና ፍትሃዊነትን አይደለም። አሁንም ሁሉን ተቆጣጥረው፤ ሁሉን ሰብረው፤ ሁሉን ጨብጠው፤ እኛ ብቻ ብለው ለመዝለቅ ያላቸው ቅዥት አልተለወጠም።ከዚህ ቅዥታቸው እስካልወጡ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሃዊነት ይመጣል ማለት እፉኚት ሆይ እርግብ ሁኚልኝ እንደማለት ነው።
የተከበራችሁ ወገኖቻችን ከእነዚህ በክፋታቸውና በጨካኝነታቸው ከታወቁ ቡድኖች የተሻለ ለውጥን አትጠብቁ።የትግራይ ነጻ አውጪዎች ጭካኔ ፈርጀ ብዙ ነው። ከደርጉ የበዛ እንጂ ያነሰ አይደለም።
በደርግ ዘመን አንድ አብዮት ጠባቂ  ልጇ የተገደለባትን ሴት ጠርቶ “የእኔ ልጅ የሥራውን አግኝቷል” ብለሽ ተናገሪ ባላት መሰረት የልጇን አስከሬን ከጎኗ ወድቆ እያየችው አዎን “ልጄ የሥራውን አግኝቷል፤ አብዮትም ልጇን ትበላለች” ብላ ተናገረች። ይሄም በቴሌቭዥንና በራዲዮ እንዲታይና እንዲሰማ ተደርጎ ነበር። በዚያን ዘመን የነበሩ ሁኔታውን ያዩ እና የሰሙ ዜጎች “ክፉ ዘመን” ብለው አዝነው ነበር።
ዛሬም  በአዲስ አበባችን በመለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትእዛዝ ልጇ የተገደለባት እናት፤ እናቷን ከገደሉባት በኋላ ቅንጅት ገደለብኝ ብለሽ ፈሪሚ የተባለችው ልጅ፤ አባትና እናታቸውን በአንዲት ጀንበር  ያጡ ህጻናት መለስ ዜናዊ አዛኝና ርሁርህ መሪ ነበረ ብላችሁ አልቅሱለት እየተባሉ ነው። ይሄ እጅግ የከፋ ጭካኔ ነው። ይሄ በቃላት ልንገልጸው የማንችለው ንቀት ነው። ለገዳዩ አልቅሱለት የሚሉ ኃይሎች ከገዳዩ የከፋ በደል እየፈጸሙ መሆናቸውን አጥበቀን ልንነግራቸው እንፈልጋለን። እንዲህ ዓይነቱን ግዳጅ በህዝቦች ላይ የምትጥሉ የነጻነት ጎህ የሚቀድበት ዘመን እሩቅ እንዳልሆነ አሁን እንነግራችኋለን። እናም ለራሳችሁ ስትሉ ከእውነትጋር እንድትቆሙ እንመክራችኋለን።
ኢትዮጵያዊያን ለሃያ አንድ ዓመት አልቅሰዋል። ዛሬ ደግሞ ሲያስለቅሳቸው ለነበረው ግለሰብ እና ቡድን ድንኳን ተክለው፤ ጥቁር ለብሰው እንዲያዝኑ እንዲያለቅሱ ታዘዋል። እንዲህ ዓይነቱን የልቅሶ ሥርዓት በሰሜን ኮሪያ ሲለቀስ አይተን ህዝቡ የታሰረበትን ጠንካራ ሰንሰለት አይተን አዝነን ነበር።ዛሬም ይህ አገሩን ሁሉ ሰብስብሶ የሚያስለቅስ ቡድን በኢትዮጵያችን ታየ። ህዝቡን በጠንካራ ሰንሰለት አስረው ግለሰባዊ መብቱን አሳጥተው፤አገሪቷን መቀመቅ ውስጥ ከቶ ዜጎቿን ለስደትና ለችጋር ለዳረገው ግለሰብ አልቅሱለት የሚሉ ሃይሎች በአገሪቷ ራስ ላይ ቁጭ ብለው መለስ ሞተ ማለት አይቻልም። አዎን መለስ አልሞተም። አዎን መለስ በህይወት አለ።
የተከበራችሁ የአገራችን ሰዎች አገራችንን ከእፉኝት ልጆች እጅ ለማዳን ግዜው ደርሷል። አሁን ለነጻነት፤ ለፍትህ፤ ለእኩልነት እና ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስትሉ ትግሉን ተቀላቀሉ። እኛ የጀመርነውን ትግል አጠናክረን እየቀጠልን ነው።ኑ ተቀላቀሉንና ራሳቸውን “ወርቅ” ብለው ጠርተው ኢትዮጵያችንን ከሚያዋርዱ ግብዞች እጅ አውጥተን ነጻነት የሰፈነባት፤ ዜጎች ሁሉ እኩል የሆኑባት፤ ፍትህ የሰፈነባት አገር እና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንገንባ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!

No comments:

Post a Comment