Translate

Saturday, September 8, 2012

በጎ ምክር ለጓዶች (ተስፋዬ ገብረአብ)


ከተስፋዬ ገብረአብ
የኢህአዴግ የስልጣን ሽኩቻ ተባብሶ በመቀጠሉ የአመራር አባላቱ ዝግ ስብሰባ ላይ ስለመሆናቸው እየተሰማ ነው። ይህን ሽኩቻ ከህዝብ ጆሮ ለመሰወር ሲባል ስለ ኢህአዴግ ስራ
Tesfaye Gebreab Ethiopian author and writer
ተስፋዬ ገብረአብ
አስፈፃሚ ስብሰባ በቴሌቪዥን የተላለፈው ቀሽም ድራማ ነበር። የአመራር አባላቱ እጃቸውን እያወጡ ድምፅ ሲሰጡ በቲቪ ይታያል። በምን ጉዳይ ላይ ነው ተከራክረው በድምፅ ወሰኑት? አልተገለፀም። ከኢህአዴግ ነባር ልምድ አንፃር፣ ከስብሰባው በፊት ጋዜጠኞች ገብተው ምስል ቀርፀው እንዲወጡ እንደሚደረግ አውቃለሁ። ከዚያም በሮችና መስኮቶች ተዘግተው ስብሰባው ይቀጥላል።
ሆነው ሆኖ፣ የመለስ ሞት ከተጠበቀው ጊዜ ፈጥኖ የመጣ ነበርና ጓዶች ያልተዘጋጁበት ገጥሟቸዋል። መለስ ጷግሜ ላይ ወደ አገርቤት ተመልሶ ለእንቁጣጣሽ ዋዜማ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፣ እስርቤቱን ባዶ ያደርገዋል ተብሎ እየተጠበቀ እሱ ግን  እንደወጣ ቀረ። እንግዲህ ህይወት መቀጠሏ አልቀረም።  በችግር ጊዜ መረዳዳት ያለ ነውና፣ የቀድሞ ጓደኞቼ ምናልባት ከሰሙኝ አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮችን እዚህ ላስቀምጥ።

የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ለሃይለማርያም ከመስጠት የተሻለ ምንም አማራጭ የለም። በዚህ ጉዳይ ላይ ልዩነቶች እየጠበቡ ስለመጡ ይህ ችግር አይመስለኝም። ርግጥ ነው፣ ሁሉም የአባል ድርጅቶች ሃይለማርያምን የሚፈልጉበት የየራሳቸው ምክንያት አላቸው። በጥቅሉ ግን ‘ቢያንስ ሃይሌ አይከዳም።’ ተብሎ ይታሰባል። ሃይለማርያም ወንበሩን የሚረከብ ከሆነ የራሱን ካቢኔ ለመቋቋም መጠየቁ መረጃ አለ። መረጃው ግን አጠራጠሮኛል። ሃይሌ ከጀርባ የሚገፋው ከሌለ ብቻውን ያን ያህል አይዳፈርም። ስለቡድን አሰራር ደህና አድርገው አጥምቀውታልና፣ በአንጋፋዎቹ እየተመከረ ስራውን ሊሰራ ራሱን አሰናድቶአል። በባህርይው ለስላሳ በመሆኑ ትእዛዝ ይጥሳል ተብሎ አይጠበቅም። ህወሃት ሃይለማርያምን በደንብ እየተቆጣጠረ ለማሰራት፣ ከአንጋፎቹ አንዱን አማካሪ አድርጎ መሾም ነው። አርከበ እቁባይ፣ አባይ ፀሃዬ፣ ስዩም መስፍን የሚሉ አሉ። በውጭ ግንኙነት ልምድ ስላለው ስዩም ይሻላል። አባይ ፀሃዬ የጀመረውን ይጨርስ። በተለይ የዋልድባ ነገር ከስኳር ምርቱ ይልቅ ከጎንደር – ትግራይ ድንበር ጋር የተያያዘ የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ስላለበት፣ ያንን ዳር ማድረስ ይገባልና አባይ ፀሃዬን መንካት አይገባም።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን መለያየት ይሻላል። መለስ ይህን ያጣመረው ሃይለማርያም ሁለቱንም ወንበር እንዳይሰራበት ስለሆነ፣ አሁን ይህ አወቃቀር አያስፈልግም። ስለዚህ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ብአዴን ቢወስደው ይሻላል። ብአዴን በመሰረቱ ምክትልነት ነባር ይዞታው ነው። የምክትልነት ረጅም ልምድ ስላላቸው ኮርተው ሊሰሩት ይችላሉ። የሚመደበው ምክትል ግን አማራ ቢሆን ይመረጣል። አዲሱና በረከት ምንም እንኳ በሰው እጥረት ምክንያት አማራን የሚወክሉ ቢሆኑም፣ አማራ አይደሉምና ለሃሜት ያጋልጣሉ። በእርግጥ ህወሃቶች አማራን ወደ ቤተመንግስቱ ማስጠጋት አደጋ እንዳለው እንደሚያስቡ ይገባኛል። ግን ምን ይደረግ? የህዝብ ብዛት አላቸው። ሚዲያው በእጃቸው ነው። ዳያስፖራ የነሱ ነው። ለይስሙላም ቢሆን ከዋና ዋና ስልጣኖች ቢያንስ አንዱን ማግኘት አለባቸው። የሚመደበው ሰው ሃይለማርያም ላይ ተፅእኖ እንዳያደርግ ባይሆን አንድ ደከም ያለ አማራ ፈልጎ ማስቀመጥ ይሻላል። ቴዎድሮስ አድሃኖምን በምክትልነት ማምጣት በጣም አደገኛ ነው። “ህወሃት መከላከያና ደህንነትን መያዙ ሳይበቃው፣ ሃይለማርያምን ከታችና ከላይ አፍኖ ጨፈለቀው” የሚል ሃሜት ሊያስነሳ ይችላል። ስለዚህ ምክትሉ ከአማራ ቢሆን ይሻላል። ለምሳሌ ትምህርት ሚኒስትሩ ደመቀ ጥሩ ምርጫ ነው። ደመቀ እንደ ስሙ ደማቅ አይደለም። ዝም ያለ እንደመሆኑ፣ ሳያስቸግር የታዘዘውን ሊሰራ ይችላል። ሽሙጥ አይደለም፣ በጎ ምክሬን ስሙ!
ውጭ ጉዳይ ለኦህዴድ ቢሰጥ የሚል አሳብ አለኝ። ኦህዴድ ሲባል መቸም አሁን ፊትለፊት የሚታየው ግርማ ብሩ ነው። ግርማ ደግሞ አይታመንም። ልቡ አሁንም ከኢህአፓ ጋር ነው። መለስም እንዲሁ እንደጠረጠረው አለፈ። በማንኛውም ቀን ሊከዳና ዱብ እዳ ሊያፈነዳ ይችላል። ስለዚህ ግርማን ራቅ አድርጎ ማሰራቱ ይሻላል።
ምን ይሻላል ታዲያ?
ግርማ ካልሆነ ከዚያ በመለስ የተሻለ የሚባል ማን አለ? እኔም ግራ ገባኝ። ችግሩ አብዛኞቹ ኦህዴዶች ኦነግ መሆናቸው ነው። ባጫ፣ አባዱላ፣ ኩማ ይታመኑ ነበር። ውጭ ጉዳይ ይከብዳቸዋል። እንግዲህ ከኦሮሞ አምባሳደሮች አንዱን የተሻለውን ማምጣት ነው።  የውጭ ጉዳይ ምክትሉን ቦታ ግን የግድ ህወሃት መያዝ አለበት። እናም ኦሮሞውን ሚኒስትር ማንሳፈፍ። ለምክትልነቱ አርከበ እቁባይ ጥሩ ነበር። ኤርትራዊ ሆነ እንጂ ቴዎድሮስ ሃጎስም ሊይዘው በቻለ። ብርሃነ ገብረክርስቶስ ግን ከዚያ ቢነሳ ይሻላል። እሱ ሰውዬ እኔ ምኑም አይጥመኝ። ሌላ ቦታ ይፈለግለት። ያጠፋው ጥፋት በማስረጃ ቢገኝ ግን ጥቂት ጊዜ ማሰር ይመረጥ ነበር። ካልሆነ ነጋዴ ይሁን።
ሌላው ክፍት የስልጣን ቦታ የህወሃት ሊቀመንበርነት እና የኦህዴድ ሊቀመንበርነት ቦታዎች ናቸው። የህወሃት አያስቸግርም። ሚዲያዎች ሲተነብዩ እንደሰነበቱት ስዩም መስፍን ሊይዘው ይችላል። አዜብ ትቅርባችሁ። አትሆንም። አርፋ ቢዝነሷን ብትቀጥል ይሻላል። “የመለስን ራእይ የማውቀው እኔ ነኝ” ምናምን ትላለች አሉ። ደፋር ናት መቼም። ሰውዬውን አቃጥለው ካዳከሙት አንዷ እሷ ናት። ወላፈኗ ለሃገርም ተርፏል። ችግሯ መናገር እንጂ ማዳመጥ አለመቻሏ ነው። ስለዚህ ለአዜብ ምንም ቦታ መስጠት አይገባም። ለንደን አዲሳባ እያለች ትንሸራሸር። ገንዘብ ይዛለች፣ ሌላ ምን ትፈልጋለች?
በተረፈ መተካካት የሚባለውን ቀልድ መተው ነው። ለኦህዴድ መሪነት አስቴር ማሞ መታሰቧ ተሰምቷል። ይቅርባችሁ። የተበታተነውን ኦህዴድ ማሰባሰብ በፍፁም አትችልም። አስቴርን ከመሾም አባዱላን መመለስ ይሻላል። አባዱላ አሁንም ቢሆን ደጋፊዎች አሉት። በመጨረሻው ግድም ደህና ስም እያገኘ ነበር። የፓርላማውን መዶሻ ከፈለገች አስቴር ትውሰደው። አስቴር ካልፈለገችው፣ ልምድ ስላለው ተሾመ ቶጋ ይመለስበት።
ሳሞራና በረከትን ኮሽታ ሳይሰማ ማንሳት ይሻላል።
ሳሞራ ቢነሳም ባይነሳም ብዙ የሚጨንቀው አይመስለኝም። ኤክስፖ ላይ ሃውልት ቆሞለታል። የሙሉ ጄኔራልነትን ማእረግ አጊኝቶአል። ምን ቀረው? ጠቅላይሚኒስትርነቱን እግሩ ላይ ወድቃችሁ ብትለምኑትም አይወስደውም። ጀብደኛ እንደመሆኑ ወታደርነት ነበር የሚስማማው። ስለሳሞራ ብዙ መፃፍ እየፈለግሁ ሁልጊዜ እረሳዋለሁ። ኤርትራ ብዙ ዘመዶች አሉት። ሳሞራ (መሃመድ) ያደገው ግን አስመራ ሳይሆን አክሱም ነው። ልጅ እያለ አክሱም ፅዮን ማርያም ቤተክርስቲያን እየገባ፣ “አላሁዋአክበር!!” እያለ ቄሶችን ማበሳጨት ይወድ ነበር አሉ። ይህችን ታሪክ ስሰማ በጣም ነው የሳቅሁት። እንዲህ ያሉ ኮሚክ ብሽሽቆች ቀልቤን ይሰርቁታል። ሳሞራ ደግ አደረገ። እነሱስ ቢሆኑ አክሱም ላይ መስጊድ እንዳይሰራ ለምን ይከለክላሉ? የሆነው ሆኖ ጀብደኛው ሳሞራ ይብቃው። ደክሞታል፣ ይረፍ።
በረከት ግን ምን ይሆናል? እንደሚሰማው ገንዘብ የለውም። ከመፅሃፍ ሽያጭ የተገኘችው ለምንም አትሆን። ባለቤቱ ዱባይ መነገድ ጀምራለች ቢባልም፣ ከመሸ ሆነ። ብቻ አላሙዲ ጓደኛው ነው። ዝም አይለውም ይሆናል። ለረጅም እረፍት ወደ ሲሸልስ ደሴት ወይም ወደ ዛንዚባር ቢልከው ጥሩ ነው። የድንበር ውዝግቡ ቢቋጭ እንኳ፣ ምፅዋ ሄዶ ማረፍ በተሻለው። “መለስ አንድም ቀን ሳያርፍ አረፈ” የሚባል አባባል አለ። በምርጫ 97 መሸነፉን ቢያምን ኖሮ ግን የማረፍ እድል ያገኝ ነበር። በረከትም ሁዋላ፣ “አንድም ቀን ሳላርፍ አረፍኩ” ምናምን እንዳይለን ካሁኑ ቢያርፍ ይሻለዋል። “ኤርትራዊ ሆኖ የአማራን ድርጅት ይመራል” እያሉ ከሚያሳብዱት ሁሉን እርግፍ አድርጎ ቀሪ ህይወቱን በፀጥታ ማሳለፍ በተሻለው። እንደ መለስ ዜናዊ የደመቀ ሽኝት ያጋጥመኛል ብሎ ማሰብም አያዋጣም። መለስ የገዛ ቀብሩን ቢያይ በጣም በተገረመ ነበር።
የሆነው ሆኖ ጓዶች! ይቺ ምክር ከጠቀመች ያዟት። መልካም አዲስ አመት።
ቢሾፍቱ ሆይ! በሩቁ ሰላም ላንቺ ይሁን…

No comments:

Post a Comment