Translate

Friday, September 7, 2012

ጊዜ የለንም፤ እንፍጠን፤ እንደራጅ! እንታገል!!!


መለስ ዜናዊ ሞቷል፤ ተቀብሯልም።
በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ለጆሴፍ ስታሊን እና በአሁኗ ሰሜን ኮሪያ ለኪም ጁንግ-ኡን ከተደረገው አምልኮተ- ሰው በላይ ለመለስ ዜናዊ ተደርጎ ታዝበናል። በሶቭየት ኅብረት፣ በቻይና እና በሰሜን ኮሪያ እንደነበረው ሁሉ፣ እኛም አገር፣ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ይገባው የነበረው ወንጀለኛ “ጀግና” ተብሎ ተወድሷል። በሌሎች አገራት እንዳየነው ሁሉ እኛም አገር፣ የተበደሉት ለበዳያቸው ሲያለቅሱ ታይተዋል፤ የተራቡትና የታረዙትም ለረሃብና ለእርዛት ለዳረጋቸው ሰው ሲያነቡ ተስተውሏል።
አምባገነኖች የገነቡት ሥርዓት እስቀጠለ ድረስ በሕይወት እያሉም ሆነ ሲቀበሩ የሚወደሱ፤ በርካታ ሃውልቶች የሚቆምላቸው፤ መንገዶች፣ ድልድዮችና ተቋማት በስማቸው የሚሰየሙ ቢሆንም፤ አስከሬናቸው እንደ ሙዚየም እቃ ለሕዝብ እይታ ቢዘጋጅ እንኳን ከታሪክ ተወቃሽነት አያመልጡም። ስታሊንን ለመሰሉ አምባገነኖች ብዙዎች መዝፈናቸው፤ ሲሞቱም ማልቀሳቸው በስፋት የሚታወቅ ነገር ነው። እነዚህ ሰዎች በታሪክ የሚታወሱት ግን በክፉ ተግባሮቻቸው ብቻ ነው። የመለስ ዜናዊ  እጣ ፈንታም ተመሳሳይ እንደሚሆን ጥርጣሬ የለንም።

በእርግጥም ዘረኛው መለስ ዜናዊ አልፏል። እሱ የተከለው ዘረኛ አገዛዝ ግን በቦታው ነው። መለስ ዜናዊ ሞቶ ቢቀበርም አገዛዙ አልሞተም። እንዲያውም በንቃትም በብቃትም ከእርሱ የደከሙ መሆናቸውን አይቶ ያስጠጋቸው፤ ሕዝብን ለመበደል ግን ከእርሱ የማይተናነሱ፤ ዘረፋ የሕይወታቸው ግብ ያደረጉ የገዢ ቡድን አባላት በቡድን በመደራጀት የመንግሥትን ሥልጣን የሚይዙበት እድል ተፈጥሯል። ለጊዜው በትምርስ ላይ ያሉት ገዢዎች የግጭታቸው ምንጭ “እኔ አስበልጬ ልብላ” ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰድን፣ ይህንን ሽኩቻ አሸንፎ የሚወጣው ቡድን ከቻለ በቀጥታ ካልሆነም ከፊት ለፊት ምስለኔ አስቀምጦ ኢትዮጵያን ማዳከሙ፣ መመዝበሩና፣ መበደሉን ይቀጥላል። ይህ ሁኔታ አገራችን ኢትዮጵያን ከመለስ ዜናዊ የግለሰብ ቀጥታ አገዛዝ የባሰ ወደሆነ የቡድን አገዛዝ ሊያስገባት ይችላል።
ይህ እንዳይመጣ መፍትሄው ምንድነው?
ከግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ስትራቴጂያዊ ግቦች አንዱ “ሰላማዊ፣ ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ የሕዝብ ምርጫ ብቻ የመንግሥት ሥልጣን የሚያዝበት ሥርዓት ማስጀመር” ነው።  የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪዎቹን በሰላማዊ፣ ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እስካልመረጠ ድረስ ነፃነቱን፣ እኩልነት፣ ሰላምና ዘላቂ ልማት ሊያረጋግጥ አይችልም። ይህን ግብ እውን እስካላደረግን ድረስ ገዢዎቻችን ቢቀያየሩም እንኳን እጅግም ለውጥ አናይም። ስለሆነም መፍትሄው፣ ያስቀመጥነውን ግብ ማሳካት ነው።
ከላይ የተጠቀሰው የግንቦት 7 ግብን ለማሳካት ከተቀመጡት አራት መለስተኛ ግቦች የመጀመሪያው “ወያኔንና ግብረ አበሮቹን ከላይ ለተቀመጠው የመንግሥት ሥልጣን አያያዝ ተገዢ እንዲሆኑ ማስገደድ ካልሆነም ከሥልጣን ማስወገድ” የሚል ነው። ይህንን መለስተኛ ግብ ተግባራዊ ማድረግ በእጃችን ውስጥ ያለ አጣዳፊ ተግባር ነው።
  • ወያኔን ማስገደድ ወይም ማስወገድ ማለት ምን ማለት ነው?
  • ማነው ነው ወያኔን የማስገደድ ወይም የማስወገድ ሥራ የሚሠራው?
  • እንዴት ነው ይኸ ሥራ የሚሠራው?
  • መቼ ነው ይኸ ሥራ የሚሠራው?
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእነዚህና ተመሳሳይ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚፈልግ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ለእነዚህ ጥያቄዎች ዝርዝር ምላሽ መስጠት ትግሉን ከሚጠቅመው ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል በሚል ብዙ ጊዜ ማብራሪያ ሳይሰጥባቸው ተሸፋፍነው ሲታለፉ ቆይቷል። አሁን የምንገኝበት ሁኔታም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በግልጽ መነጋገር የሚያስችለን አይደለም።
ይሁን እንጂ ግንቦት 7 በእነዚህ እና መሰል ጥያቄዎች ላይ በጥልቀት አስቦ የተነሳ ድርጅት መሆኑ አበክሮ መግለጽ ይፈልጋል። የትግል ስልቱንም “ሁለገብ” ብሎ ሲሰይምም የሰላም አማራጭ ሳይዘጋ ሌሎች አማራጮችንም ለመፈለግ ካለው ፍላጎት በመነሳት ነው።
ግንቦት 7፣ ወያኔን የማስገደድ ወይ የማስወገድ ሥራ መከወን ያለበት በሁሉም ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ትብብር እና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ነው ብሎ ያምናል። በዚህም ምክንያት ነው ግንቦት 7  በመርህ ላይ ለተመሠረተ ትብብር ትኩረት ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ የቆየው። እንደ ግንቦት 7 እምነት ወያኔ የሚወገደው በሁሉም ቦታ እና በሁሉም ዘርፍ በሚደረግ ሁለገብ ትግል ነው። ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ሌላው በእለት ተእለት ተግባሩ ሳይቀር ወያኔን መታገል ይቻላል፤ ይገባልም። ለምሳሌ ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን እንዳደረጉት ሁሉ የሃይማኖት ተቋሞቻችንን የነፃነታችን ማወጃ ቦታዎች ማድረግ እንችላለን፤ ይገባልም።
ባጭሩ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሁለገብ ትግል የሚያበረክተው ነገር አለ።
ትግላችን በተደራጀ መልክ መፈጸሙ ለስኬታችን ወሳኝ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄን እንዲቀላቀሉ እንጠይቃለን።
በመጨረሻም ይህ ትግል መደረግ የሚኖርበት ዛሬ መሆን እንዳለበት አበክረን ማስገንዘብ እንወዳለን። አሁን ወያኔ አውራውን አጥቶ በመደናበር ላይ ነው። በዚህ ወቅት ላይ ለውጥ ካላመጣን ከላይ እንደተገለጸው ከመለስ ዜናዊ የባሱ ዘረኞችና ሙሰኞች መድረኩን ሊቆጣጠሩ ይችላሉ።
ስለሆነም ጊዜ የለንም። እንፍጠን። እንደራጅ! እንታገል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment