Translate

Monday, September 3, 2012

ሃይለማርያም ደሳለኝ - ማንነት እና ፖለቲካዊ ሰብዕና

HaileMariamየአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፤ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር (?) ፖለቲካዊ ሰብእና ብዙ የሚታወቅ ባለመሆኑና፤ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ግን በቅርብ ርቀት የሚያውቃቸው ሰው በመሆናቸው ይህችን አጭር ፅሁፍ ለመፃፍ አነሳሳኝ። አቶ መለስ ዜናዊ ካወረሱን ቅርሶች አንዱ “የዘሬን ያንዘርዝረኝ” ነውና፤ የአቶ ሀይለማርያምን ፖለቲካዊ ሰብእና ስተርክ ከዘር ብጀምር አይፈረድብኝም። ሀይለማርያም ደሳለኝ እንደ ዳግማዊ አፄ ሚኒልክ በእናታቸው ብቻ ሳይሆን፤ ሙሉ በሙሉ (በእናትም በአባትም) በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኙት 48 ብሄረሰቦች መካከል አንዱ የሆነው የወላይታ ተወላጅ ናቸው። የወላይታ ብሄረሰበ ህዝብ ብዛት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋና፤ ከኢትዮጵያ ህዝብም 3% ያህል የሚሆን ነው። ሀይለማርያም ደሳለኝ በእምነታቸው ፕሮቴስታንት (የፔንቴኮስታል ክርስቲያን) ሲሆኑ፤ በመንፈሳዊ ህይወታቸውም የሚፀልዩና መፅሀፍ ቅዱስ የሚያነቡ ትጉህ ሰው እንደሆኑ ብዙ ሰዎች ይመሰክሩላቸዋል። ከዚህ እምነታቸውም የተነሳ ሊሆን ይችላል፤ እንደ በርካታ የአቶ መለስ ባለስልጣናት በሙስና (corruption) ውስጥ አልተዘፈቁም። አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ለህወሃት- ኢህአዲግ የድል አጥቢያ አርበኛ ሰው ናቸው። ማለትም እንደነ አቶ መለስ ለ17 አመታት በበረሃ ታግሎ የመጣ ሰው ሳይሆን፤ ከግንቦት 20 ቀን 1983 ድል በሁዋላ ኢህአዴግን በአባልነትና በደጋፊነት የተቀላቀለ ሰው በሙሉ የ“ድል አጥቢያ አርበኛ” ስለሚባል ነው።
ሀይለማርያም ደሳለኝ እድሜው በአርባዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኝ፤ በትምህርት ዝግጅቱም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንጀሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪና፤ ከአውሮፓም ሁለተኛውን ዲግሪውን በኢንጂነሪንግ ዘርፍ የያዘ ሰው ነው። የሙያ ልምዱም በማስተማር፤ በኮሌጅ ሃላፊነት፤ በደቡብ ክልል አስተዳዳሪነት ወይም ፕሬዜዳንትነትና፤ በጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ በሚንስትር ማእረግ አማካሪነት እና በቅርቡም የውጭ ጉዳይ ሚንስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ዋነኞቹ ናቸው። ሰብዕናውን በተመለከተ፤ ሀይለማርያም ቅን ትሁትና ሰውን አክባሪ፤ ምሁርና ተግባቢ፤ በራሱ የሚተማመን፤ ስብሰባ ሲመራም ሆነ ሀገር ሲያስተዳድር የማይናደድ፤ የማያስፈራራና የማይደነፋ፤ ተቃራኒ ሀሳብ የሚቀበልና ባግባቡ የሚመልስ፤ የበታችነት ወይም የበላይነት ስሜት የማይሰማው፤ በአግብኦ፤ በአሽሙር ወይም በሽሙጥ የማይናገር፤ ፈገግታ የማይለየውና ለማነጋገርም የማይከብድ ሰው መሆኑን እመሰክራለሁ። ከሁሉ በላይ ደግሞ የአቶ ሀይማርያም ትልቁ ሰብእና የኢህአዲግ ባለስልጣንም ወይም ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር ቢሆንም ባይሆንም፤ ራሱን ችሎ፤ በሰላምና በነፃነት ለመኖር እንደሚችል የተረዳ ሰው መሆኑ ዋናው ሲሆን፤ አንባገነን ልሁን ቢልም ለመሆን የማይችልም ይመስለኛል። በነዚህ ዋና ዋና ባህርያትና እንዲሁም አቶ መለስ ዜናዊ ኦሮሞዎችንና አማራዎችን ለጠቅላይ ሚንስትርነት ስልጣን ባለማመናቸው ምክንያት አቶ ሀይለማርያምን ወደ ቤተመንግስታቸው ያስጠጉዋቸውም ይመስለኛል። በእኔ መረዳትና ግንዛቤ፤ የአቶ ሀይለማርያም ትልቁ ድክመት ሊሆን የሚችለው ደግሞ፤ ሀይለማርያም አፍተልታይ ፖለቲከኛ ያለመሆናቸው ጉዳይ ዋናው ይመስለኛል። ለምሳሌ፤ ከበድ ያለ ውሳኔን ለመወሰን፤ የተሸረበ ፖለቲካዊ ነገርን አለመለየት፤ የህወሐት አንባገነን ሰዎች ጫና ለመቋቋም አለመቻል፤ ሰዎችን ለማግባባት ሲሉ የመዘግየትና የመፍራት ችግር ሊኖርባቸው ይችላል የሚል ግምት አለኝ። እንደዚሁም ነገር-አዋቂና ሰንጣቂ፤ እጅ-ጠምዛዥና አስጠምዛዥ፤ ትንሽ ቢሆን ተጠራጣሪም ሰው ባለመሆናቸው ከህወሀት-ኢህአዴግ አድርባይ፤ ቀንጨራ፤ እና ተንኮለኛ ሰዎች ጋር እንዴት ተግባብተው ሊሰሩ እንደሚችሉ ሳስብ ግርታ ይፈጥርብኛል። በአጠቃላይ አቶ ሀይለማርያም ከመሪነት ይልቅ ወደ አሰተዳዳሪነት የሚያደሉ ሰው እንጂ፤ የፖለቲካ ሴራ እየሸረቡ፤ ሰኞን ማክሰኞ ነው፤ ድንጋዩን ዳቦ ነው፤ ጭለማውን ብርሀን ነው፤ እያሉ አይናቸውን አፍጥጠው እየዋሹ በስውር፤ በማስመሰል ለመኖር የሚችሉ ሰው አይመስለኝም። እንደዚህም ስል ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ለመስራት ይቸገራሉ የሚል ስጋት ግን የለኝም። የዘር የፖለቲካ ስልጣን በተመለከተም፤ ዘርን በጣም አንዘርዝረን ካየነው ደግሞ የአፄ ሚኒልክና የአቶ ሀይለማርያም ዘር ከወላይታ መሆን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስልጣን ከአማራና ከትግሬ በመቀጠል የሀገር መምራት ስልጣን በመረከብ ወላይታዎች ሶስተኛ ደረጃ ሆነዋል ማለት ነው። ምንም እንኳን አቶ ሀይለማርያም ሚኒልክ ቤተመንግስት በመግባት በእናታቸው ወላይታ ከሆኑት ከአፄ ሚኒልክ ቀጥሎ ሁለተኛው የወላይታ ተወላጅ ቢሆኑም፤ ስልጣኑን በችሮታ እንጂ፤ በምርጫ ወይም በትግል ያገኙት ባለመሆኑና፤ በአሁኑ ሰአት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስልጣን ባላንጣ ከሆነው ከህወሀት የፖለቲካ አጥር ክልል ውጪ መጫወት እንዳይችሉ ሆነው የተቀመጡ መሆናቸውን በቅርብ የምናየው ይሆናል። ይህ እውነት ከሆነም ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እኩል የሚጠቅም አኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት በጣም የሚቸገሩ ሰው ስለሚሆኑ በስልጣን ላይ የሚቆዩ አይመስለኝም። አለበለዚያ በስልጣን ለመቆየትም የአቶ መለስ ዜናዊን ሰብዕና ሙበ ሙሉ መላበስ ይኖርባቸዋል። ከዚህ ውጭ ከተመለከትንና የሚሆንም ከሆነ ደግሞ እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ፈፅሞ ሊታደግ በጊዜው ያስቀመጣቸው የመጀመሪያው ረድኤተ መሪ ሆነው ብቅ የሚሉ መልዕክተኛ ሆነው ይወጡ ይሆናል። ሃይለማርያም ደሳለኝ ዳግማዊ አፄ ሚኒልክም ወላይታ ወደ መሆናቸው ጉዳይ ስንመጣ ንጉሰ ነገስት ሚኒልክ በእናታቸው ወላይታ እንደሆኑ እጅግ አብላጫ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን የሚያውቁት አልመሰለኝም። ይህችን መጣጥፍ የዳግማዊ አፄ ሚኒልክና የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የዘር ግንድ አንድ ነው ብዬ ርዕስ የሰጠሁትም ለዚህ ነው። ታሪኩ ባጭሩ እንዲህ ነው። የአፄ ምኒልክ አያት ንጉስ ሳሕለ ስላሴ በዘርዋ ወላይታ የሆነች የቤት ሰራተኛ ነበረቻቸው። መልካም የሆነውን ታሪክ ብቻ፤ የነገስታትንና የጦርነት ታሪክ ብቻ የሚተርኩልን ተወቃሽ የታሪክ ፀሀፊዎቻችን፤ ሌላውን ታሪክ እንደሚዘሉ ሁሉ፤ የሚኒልክ እናት የሆነችውን የዚህችን ብልህ ወጣት የቤት ሰራተኛ ታላቅ ታሪክ በመዝለል አልፈውታል። ነገር ግን እውነት እውነት ናትና ልትደበቅ አልቻለችም፤ በተለያዩ ታሪካዊ ፅሁፎች ላይ ሰፍራለች። በርግጥ ድሮም ቢሆን፤ በሀገር መሪዎች ህይወት ዙሪያ የተደበቀውን ምስጢር፤ አገሬው፤ ገበሬው በስፋት የሚያውቀውና ህዝቡ በአፈ ታሪክነት ሲቀባበለው እየቆየ እዚህ ከደረሱት ታሪኮች አንዱ ይኸው የሚኒልክ እናት ወላይታ የመሆንዋ ታሪክ ነው። ብልህዋ የወላይታ ተወላጅ የዳግማዊ አፄ ሚኒልክ እናት የሰራችው ታሪካዊ ስራ እና በኢትዮጵያ የአንድ ዘር ፖለቲካን በመቀየጥ ያመጣችው ታላቅ ለውጥ እንደሚከተለው ነው። ይኸውም ይህችው አስተዋይ ወጣት ለንጉሱ ባለሟል ከብልቴ ፀሀይ ሲወጣ በህልሜ አየሁ ብላ በመናገርዋ የተነሳ፤ ባለሟሉም ይህን ጉዳይ አስገርሞት ለንጉሱ ተናግሮ ኖሮ፤ ንጉሱም ብልህ ናቸውና ሊሆን የሚችለውን በትንቢት በማስመርመርና በመገመት ልጃቸውን (በሁዋላ ንጉስ የሆነውን) ሀይለ መለኮትን እዚህች ልጃገረድ የቤት ሰራተኛው ላይ እንዲደርስባት (እንዲገናኛት) አስደርገው ሀይለኛውና፤ አሰተዋዩ ዳግማዊ አፄ ሚኒልክ ሊወለድ ችሏል። ጊዜውን ጠብቆም እምዬ አፄ ሚኒልክ ተብሎ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት በመሆን፤ ቅኝ ገዢዎችን በአድዋ ድል በማባረር፤ ብቸኛው ጥቁር የአፍሪካና የኢትዮጵያ ኩራት ሆነ። ታላቁ የኢትዮጵያ መሪ ዳግማዊ አፄ ሚኒልክ በአባቱ አማራ ቢሆንም በእናቱ ንፁህ ወላይታ መሆኑን ዛሬ ሀይለማርያም ደሳለኝ ከወላይታ ዘር ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆኑ የተፈበረከ ታሪክ ያለመሆኑ ታሪክን ብንመርምር እንደርስበታለን እላለሁ። ቸር እንሰንብት እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ

http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_lyftenbloggie&view=entry&year=2012&month=09&day=03&id=65%3A2012-09-03-16-14-31&Itemid=11

No comments:

Post a Comment