Translate

Saturday, September 8, 2012

የወ/ሮ አዜብ ሥላቅ


(ወገ ሹኩቻ እና የአዜቧ አቛም ፡-  ወ/ሮ አዜብ የቱ ጋ ናቸው?… ለሁሉም ግን ተዘባበቱብን)

( ተፃፈ በወፉ 9/5/2012)
Azeb Mesfin, the wife of Meles Zenawiወ/ሮ አዜብ ከሁለት ልጆቻቸው ጋር በህዝብ ፊት ቆመው ያደረጉት ንግግር ስሜት የሚነካ መሆኑን ባይካድም ተራ የፖለቲካ ሸፍጥ የሚመስልም እንደነበረ ሁሉ ይገነዘበዋል የሚል ፅኑዕምነት አለኝ፡፡ ወ/ሮ አዜብ ስሜት በጎዳው ንግግራቸው እና አስበው ያፈለቁት ሃሳብ እጅግ የሚያሳዝን ቢሆንም ንግግራቸው ውስጥ ግን ሸፍጥ፤ ክደት፤ የተራከሰና በስክነት ያልታሰበ ፖለቲካ ጣል አድርገዋል፡፡ ሙት ወቃሽ አያድርገኝና ባለቤታቸው የተዘባበቱበትን የህዝብ ዳኝነት ጉዳይ ወ/ሮዋም አንስተው ተሳልቀውብናል፡፡
በመጀመሪያ የወ/ሮ አዜብ ስብዕና ወይንም የአማራ ትግሬነት ደም ቅየራ እንዴት እንደተከናወነና በማን ተንኮል ተበርዞ እንደተሰራ ከወ/ሮ አዜብ ከ30 ዓመት በላይ ቆይታ በኋላ ተገልፆልናል፡፡ ብዙዎች እንደሚሉት እና ወ/ሮ አዜብ እራሳቸው እንደመሰከሩት ወደ ትግል ሜዳ የገቡት ትንሽ ልጅ ሆነው ነው፡፡ ወጣት ሳልሆን ገና ትንሽ ልጅ እያለሁ መለስን አወቅሁት ይሉናል፡፡ የዘረኝነት ኮብራ ወ/ሮ አዜብን የነደፋቸው በዚያን ጊዜ ነው፡፡
ለሁሉም እኩልነት የሚታገሉት መለስ የትግሬን የበላይነት የከተቧቸውና ጎንደሬነታቸውን አስወልቀው ትግሬ ያደረጓቸው ያኔ ነበር፡፡ የወ/ሮ አዜብ ስብዕና ተጠፍጥፎ የተሰራው በመለስ መሆኑን ለመገንዘብ ጥቂት ሃሳብ ላንሳ፡፡ መለስ በፍቅር ፍቅረኛቸው ነበር፡፡ ስለዚህም መለስ ልባቸውን በፍቅር ሰልቦታል፡፡ ሁለተኛው አስተማሪየ ነበር አሉ፡፡ መለስ የአዜብን ጭንቅላት (አዕምሮ)በከባዱ አቅጣጫውን አስቶታል፡፡ በተምታታው ቅጥ አንባሩን በጠፋው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፤ሌኒንዝም፤ ልማታዊ ዲሞክራሲ፤ ጥገኛ ፤ትምክህተኛ እያለ በጭንቅላታቸው ላይ ተጫውቷል፡፡ ወ/ሮ አዜብ አስተማሪየ ነው ከማለታቸው በላይ የመለስ ጭንቅላት ገቢያ ያወጣልም ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ ስለዚህም አዜብ መስፍን ስብዕናም ስሜትም ጭንቅላትም ከመለስ ተቀብለዋል፡፡ አለቃየ ነበር ብለውናል፡፡ በአዜብ ላይ ስልጣን ነበረው ማለት ስለሆነ ሃይላቸውን ሁሉ የሚቆጣጠረው መለስ ነበር ማለት ነው፡፡ መለስ በመጨረሻም የአዜብ ሁሉ ነገራቸውና ሁለንተናቸው በመሆኑም በፍፁም ነፍሳቸው ሃይላቸው እና ሃሳባቸው የመለስ እስረኛ መሆናቸውን መስክረዋል፡፡ በመሆኑም ከ30 ዓመት በላይ የአንድ ሰው ሁለንተናዊ እስረኛ የነበሩ ሴት ሃዘን ተጨምሮባቸው የሚናገሩትን ማመን ቢከብድም ንግግራቸው ማጤን ግን ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጲያ ህዝብ በአንድ ቦታ በአንድ አይነት እባብ ሊነደፍ ስለማይገባው ነው፡፡
ከዚህ በመነሳት  ̋የመለስ ራዕይ እስካልተበረዘ ድረስ” ይሰመርበት ከኢትዮጲያ ህዝብ ጎን ቆሜ የበኩሌን አስተዋፅኦ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡ ከዚህ ንግግር የመጀመሪያው ጥያቄ አዜብ ከኢህዴግ ጎን የቆሙት በመለስ ራዕይ ብቻ ነው ወይንም ኢህአዴግ ራዕይ የለውም ማለት ነው የሚል ነው፡፡ አሊያም የመለስ ራዕይ ወይም ማንነት እንጂ ኢህአዴግ የለም ማለት ነው፡፡ ድሮ ድሮ ኢህአዴግ የለም ወያኔ እንጂ ይባል ነበር አሁን ደግሞ መለስ እንጂ ወያኔም ኢህአዴግም እንደሌለ ነው የምንረዳው፡፡ ወ/ሮዋ ሌላ የነገሩን ሁለተኛው ነገር  ኢህአዴግ ራዕይ እንደሌለው ሲሆን ሶስተኛው ኢህአዴግ የመለስን ራዕይ እምቢ ሊል ይችላል የሚለውን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ይህ ንግግር የሚያሳየን ኢህአዴግ መለስን ፈርቶ የመለስን ራዕይ አቤት ወዴት እያለ ይፈፅም እንደነበር ነው፡፡ አዜብ ስጋታቸውን እና ምርጫቸውን አካፍለውናል፡፡ የዚህ አስደናቂ ጎን የመለስ ራዕይ ካልተበረዘ ከኢትዮጲያ ህዝብ ጋር እቆማለሁ ማለታቸው ነው፡፡ ተመልከቱ እኒህ ሴት የሚቆሙት ከማን ጋር ነው? ከኢህአዴግ ጋር ወይስ ከኢትዮጲያ ህዝብ ጋር?  ከኢህአዴግ ጋር ወይስ ከመለስ ራዕይ ጋር ወይስ ከወያኔ ጋር? እንደግል ወይስ እንደወያኔ?  እንደ ኢህአዴግ ወይስ እንደ ወያኔ?  በአጭሩ ወ/ሮ አዜብ እያሳበቁት ያሉት መለስ ስለሌለ የባለቤቴን ራዕይና እኔን እንዳያባርሩኝ ጠበቃ ቁሙ የምትል ቅስቀሳ መሰለችኝ፡፡ ወ/ሮዋ በሃዘን ውስጥ ቢሆኑም እያወጉን ያሉት ወግ  ̋ወገ ሹኩቻ ነው፡፡”
ወ/ሮ አዜብ አቛምዎትን እንደግልም ሆነ እንደ  ፓርቲ ፖሊት  አባልነትዎ ሊለዋወጡ (እንደ ባለቤተዎ ሊገለባበጡ) ይችላሉ፡፡ ከአህያ ጋር የዋለች ላም እንዲሉ የተገለባባጩ መለስ ሚስት በመሆነዎ አልፈርድቦዎትም፡፡ ግና ማሳሰቢያው በኢትዮጲያ ህዝብ ላይ አይሳለቁበት የሚል ነው፡፡ ስላቀዎን ላሳየዎ፡-
ስላቅ 1፡-  ህዝቡ ዳኛ ነው ብሎ መለስ ያምን ነበር አሉን፡፡ ይህ ስላቅ ነው፡፡ ለ21 ዓመት አንድም ቀን የህዝቡን ሃሳብ ሲፈፅም ታይቶ አይታወቅም (በመሬት ፖሊሲ፤ በምርጫ፤ በአሰብ ወደብ፤ በፌደራሊዝም አወቃቀር፤ በትምህርት ፖሊሲ ሁሉ ጭፍን አምባገነን መሆኑን ለ21 ዓመት በህዝቡ ላይ ተፈናጦ አስመስክሮአል)
ስላቅ 2፡-  መለስ ከውስጡ ዲሞክራት ነበር አሉን ይህም ስላቅ ነው፡፡ መለስ አመባገነናዊ ገዥ ነበር፡፡
ስላቅ3፡-  ልጆቹን ለኢትዮጲያ ህዝብ ሲል አያውቃቸውም አሉን ይህም ስላቅ ነው፡፡ምክንያቱም ከቤተሰቡ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እና ምቾት እንደነበረው ከንግግረው ነቅሼ ላውጣ
-የመለስ ሞት ለእኔ መራር ጨለማ ነው፡፡ ፍቅረኛየን አስተማሪየን አለቃየንና ሁለንተናየን አጣሁ ብለዋል፡፡ ጥብቅ ግንኙነት፡፡
-ልጆቼ መካሪ አፍቃሪና ተንሰፍሳፊ አባታቸውን ስላጡ አዝነዋል ብለዋል፡፡ ልጅን ያለ አባት ያስቀረው መለስ ታምራት ላይኔን ለ12 ዓመት አስሮ ልጆቻቻውን ያለአባት አስቀርተዋቸዋል፡፡ እሱ ግን በቤተመንግስት ከልጆቹ ጋር ሲዝናና ኖሯል፡፡ ይህም ጥብቅ ግንኙነት እንደነበረው ያሳያል፡፡
ስላቅ 4፡- የእናትነት ፈተናን ብቻየን የምወጣበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት ከማን ጋር ልጆቾዎን አሳደጉ ጊዜ ከሌለው መለስ ጋር አልነበርም? ለኢትዮጲያ ህዝብ ሲል ጊዜ ለልጆቹ አልነበረውም ካሉን እና ያሉን እውነት ከሆነ እስከዛሬ ብቻዎትን ነበር ያሳደጓቸው ማለት ነው፡፡  ስለዚህ ምንም አዲስ ነገር የለም ከቤተመንግስት ግቢ ከመውጣቶዎ በስተቀር፡፡ ከኢትዮጲያ ህዝብ ጋር ከሆኑክ እወጣዋለሁ ያሉንማ ከባድ ስላቅ ነው፡፡ ምንድን ነው ከኢትዮጲያ ህዝብ የሚጠብቁት ስለ ልጆቾዎ? እናንተ የማንን ልጅ አሳድጋችሁ ነው የኢትዮጲያ ህዝብ ልጅ የማሳደግ ሃላፊነት የሚሰጠው? ይህ አገራዊ ጉዲፊቻ (ልጅን ለሃገር ሙሉ መስጠት)ከምን የመጣ ነው ሞትን ፈሩ እንዴ? ይህም ስላቅ ነው፡፡ ወ/ሮ ሙሉ የታምራት ላይኔ ባለቤት ብቻቸውን ባላቸውን አምባገነኑ ባለቤትዎ በግፍ አስሮ እያሰቃያቸው እነ ብሌንን ሲያሳድጉ የኢትዮጲያ ህዝብ አብሮ እንዲቆሙ ንግግር አላደረጉም፡፡ እውነቱን ልንገረዎት ይህን የምናገረው ልቤ እየደማ ነው ከልቤ አዝንለዎታለሁ ግን ንግግርዎ ልቦዎን አሳየኝና ይህንን አፃፈኝ፡፡ እኛን አላወቁንም፡፡ ኢትዮጲያውያን ሩሁሩሁ ነን ግና ሸፍጥ አንወድም፡፡ ሃዘኑን ፖለቲካ ሲያደርጉት የአርባ ጉጉ ሕፃናት እልቂት የ97 ምርጫ እልቂት ሌላም ጥፋት ትውስ ይለናል ፡፡
ስላቅ 5፡- መለስ ቢል ቦርድ ላይ እንዲለጠፍ አይፈልግም ነበር አሉን፡፡ ይህ ስላቅ ነው፡፡ የመለስ የስልጣን ማዕረግ ብዛት የትየሌሌ ነበር፡፡ ለ21 ዓመት በህዝቡ ላይ ተፈናጦ ገዝቷል፡፡ ከዚህ በላይ ምን ቢል ቦርድ አለ?
ስላቅ 6፡- መለስ ለእኩልነት ነው የታገለው ያሉትማ ታላቅ ስላቅ ነው፡፡ መለስን የሚያክል በዘረኛነት የሰከረ ሰው ታይቶ አይታወቅም፡፡ ፎቁ የማነው? መሬቱ የማነው? የጦር ሃይሉ ፤ ሰራዊቱ እና ዘራፊው ማነው? ጎንዴሬዋን አዜብን ትግሬ ነኝ እስኪሉ ያሳታቸው ማነው?
ስላቅ 7፡- እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ መለስ በየቤቱ ምን እንዳደረገለት ያውቃል ብለዋል፡፡ አቤት ስላቅ! ስላቅ ያደረገውን ልንገረዎት መለስ ያደረገው ሞት ውርደት ስድብና ጥፋት ነው፡፡
የእኔ ጥያቄ አሁን የኢትዮጲያ ህዝብ እንዲያውቅልዎት የፈለጉት ምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡ ፍላጎትዎ፡-
  1. ኢህአዴግ የመለስን ራዕይ ሊያስፈፅመው ካልቻለ ህዝቡ ከጎኔ ሆኖ ያምጽ ለማለት ነው?
  2. ኢህአዴግ ራዕይ የለውም ወይንም ሌላው የፓርቲው አባል ማሰብ አይችልም ብለው እየቀሰቀሱን ነው?
  3. የመለስ የጥፋት ራዕይ እንዳይበረዝ ማለትም ሰው ይታሰር ፤ዴሞክራሲ ይጥፋ፤ አማራ እና ኦሮሞ በዘሩ ምክንያት ይንገላታ፤ ትግሬ በዘሩ ምክንያት ይጠቀም ለዚህም እንታገል እያሉን ነው?
  4. የመለስ ደካማ ጎኑ ሳይበረዝ (ሳይታረም) ይቀጥል ለማለት ነው?
ወ/ሮ አዜብ ያሉት ምንድን ነው? መለስ ያሰበው እና ያለው ካለተፈፀመ አልታገልም ነው፡፡ የመለስ ራዕይ ካልተበረዘ አስተወጽኦ አደርጋለሁ ያ ካልሆነ አላደርግም ነው፡፡ ይተውታ፡፡ እንዲያውም ይረፉ፡፡ አገሪቱን መለስ መለስ እያሉ አያላዝኑባት፡፡ የእርስዎ አስተወፅኦ ለሃገሬ ኢምንት ነው፡፡ ደግሞስ እስከዛሬ ምንም ሳያደርጉ  ቆይተው ዛሬ ምን መጣና ነው የኢትዮጲያ ህዝብ ያሉን? የትግራይ ህዝብ አይሉንም? ውሸት አይደልም ሃዘንዎ ሃዘናችን ነው፡፡መለስ ለፍርድ ሳይቀርብ መሞቱ ያሳዝናል፡፡ ሰውም ስለሆንንና ስለሆነ በመሞቱ አዝነናል፡፡ ሞትንና ሃዘንን ማየታችሁ ትምህርት ቢሆንም አስከፍቶናል፡፡ እኔ ፃሃፊው በግሌ ያዘንኩት ለእርስዎ ነው፡፡ ያለቀስኩትም ተቀጣሁ እያሉ ሲያለቅሱ ባየሁ ጊዜ ነው፡፡ ሳላጋንን እየየ ብየ አልቅሻለሁ ቢሆንም ግን ወ/ሮ አዜብ ልንገረዎት በሃዘን ላይ ሃዘን ካልጨመርኩበዎት ለኢትዮጲያ ህዝብ የሚያደርጉት ብቸኛው አስተዋፅኦ (ለሃገሬ የሚያደርጉት ) እራሶዎንና ᎂች ባለቤትዎን ወክለው (ይዘው) አውቀው ባጠፉትና ሳያውቁ በሰሩት በደል ንስሃ መግባት ብቻ ነው፡፡ቸር እንሰንብት፡፡ አዜብ ሆይ  ይቆዩልንም ይረፉልንም፡፡ ( ተፃፈ በወፉ 9/5/2012)

No comments:

Post a Comment