በአይሲስ በግፍ በታረዱብን ወገኖቻችን የተሰማን ሀዘንና ቁጭት ከፍተኛ ቢሆንም እንኳን ከአዕምሮዓችን መውጣት የሌለበት ሀቅ አለ። ይህ ሀቅ “ያስጠቃን፣ ያሳረደን ወያኔ ነው” ከሚለውም ያለፈ ነው። መረሳት የሌለበት ሀቅ፣ ከአይሲስ የከፋ ጨካኝ በአገራችን የመንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠረ መሆኑ ነው።
የህወሓት ፋሽስት ጦር በበደኖ፣ በአዋሳ፣ በሀረር፣ በጋምቤላ፣ በጎንደር፣ በኦጋዴን፣ በአዲስ አበባ፣ በሸካና መዠንገር፤ እንዲሁም በሚታወቁም በማይታወቁም የማሰቃያ እስር ቤቶች አይሲስ እየፈፀመ ካለው የባሱ ወንጀሎች በወገኖቻችን ላይ ፈጽሟል፤ አሁንም እየፈፀመ ነው። ባሳለፍነው ሣምንት እንኳን በሁመራ ወገኖቻችን የራሳቸውን መቀበሪያ ጉድጓድ ቆፍረው በጅምላ ተገድለዋል። በአይሲስና በህወሓት መካከል ያለው ልዩነት አይሲስ ነውረኛና አረመኔዓዊ ተግባሩን በቪዲዮ እየቀረፀ ለዓለም ሲበትን ህወሓት ግን እነዚሁኑ ነውረኛና አረመኔዓዊ ተግባሮችን እየፈፀመ መረጃዎች አፍኖ መያዙ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ግን ህወሓት ሰዎችን ከነሕይወታቸው ጉድጓድ ውስጥ የቀበረ አረመኔ፣ እኩይ ድርጅት ነው።
ስለሆነም ለዓለም ሰላም ስጋት የሆነውን አይሲስን ስንቃወም የራሳችንን አይሲስ – ህወሓትን – አለመርሳት እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ህወሓት፣ የአይሲስን እኩይ ተግባራት ከኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ጋር እና ከዲሞክራሲያዊያዊ ፓለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ጋር ለማገናኘት እያደረገ ያለው ጥረት ምን ያህል አደገኛ ተግባር እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲረዳው ያስፈልጋል። ዓይን አውጣ ሌባ ንፁሁን ሰው “ሌባ” እንደሚለው ሁሉ የኛው አይሲስ ራሱን ንፁህ አስመስሎ ሌሎችን “አይሲስ” ማለቱ ሊነቃበት ይገባል።