ከኤርሚያስ ለገሰ (ቁጥር አንድ)
የዛሬ ሁለት አመት በጸደዩ ወራት የኢሳት ስድስተኛ አመት ለማክበር በፍሎሪዳ ግዛት ታምፓ ከተማ ተጉዤ ነበር።-የአጋጣሚ ነገር ሆኖ በዝግጅቱ ላይ ከድምጻዊ ቴዎድሮስ ጋር አብሮ የሰራ ድምጻዊ አብሮኝ ተጉዟል ። ይህ የሚወዳት አገሩን ተቀምቶ በሰሜን አሜሪካ ቨርጂኒያ የከተመ አርቲስት ጋር በነበረን ወግ መሃል ስለ አርቲስት ቴዲ አፍሮ አንስተን የተጫወትንበት ነበር። ቴዲ አፍሮን በቅርበት የሚያውቀው ይህ የኪነጥበብ ሰው እንዳጫወተኝ ከሆነ የቴዲ አፍሮ የስኬት ምክንያቶች በዘፈቀደ የመጣ አይደለም። ይልቁንስ የቴዲ የስኬት ምክንያቶች የስራ ዲሲፕሊኑ፣ ትጋቱ፣ ለራሱና ለሙያው የሚሰጠው ዋጋ፣ በየጊዜው ብቃቱን ለማሳደግ የሚያደርገው ጥረት፣ ትላንት የነበረውን አስተሳሰብ ዕድገት ለማምጣት ያለው ዝግጁነትና የጠለቀ የአሸናፊነት ስሜት ሰንቆ መጓዙ እንደሆነ ያምናል። በህይወቴ ጥንቅቄ የሚያውቅ እንደ ቴዲ አፍሮ አላጋጠመኝም ይላል።