በህወሃት የታፈነው ድርቅ ወደ ረሃብ እያደገ ነው፤ ት/ቤቶች ተዘግተዋል!
- የኢትዮጵያ ሶማሌ ዘጠኙም ዞኖች ሙሉ በሙሉ የድርቁ ሰለባ ሆነዋል!
- በክልሉ 437 የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከድርቁ ጋር በተያያዘ ተዘግተዋል፤
- 183,090 ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል!
- የእርስበርስ ዕልቂት ያሰጋል!
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሁለት ወራት ውስጥ ባወጣቸው ተከታታይ ሪፖርቶች ምስራቅ አፍሪካ የከፋ ድርቅ መከሰቱንና ዓለም የዕርዳታ እጆቹን ለአገራቱ እንዲዘረጋ በተከታታይ ሪፖርቶቹ ተማጽኗል፡፡ እንደ በዘገባው ከሆነ ድርቁ የከፋባቸው ተጠቃሽ አገራት ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያና ኢትዮጵያ ናቸው፡፡
ከኢትዮጵያ ውጭ የተጠቀሱት መንግሥታት ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የዕርዳታ እጃቸውን በመዘርጋት፤ በተባበሩት መንግሥታት በኩል የአውሮጳ ህብረትና ሌሎች ለጋሾች በከፋ ድርቅ ላይ ለሚገኙት አገራት ዕርዳታ እየሰጡ ናቸው፡፡ በተባበሩት መንግስታት ሪፖርት መሰረት አገራቱ በእርስበርስ ጦርነት የሚታመሱ እና በውስጥ ችግራቸው የፖለቲካ አለመረጋጋት የሚታይባቸው የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች የነገሰባቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም ድርቁ ዜጎቻቸውን ለስደት ከመዳረግ አልፎ አገራቱን ለከፋ ማህበራዊ ቀውስና ለውስጥ አለመረጋጋት እየዳረጋቸው እንደሆነ ሪዘገባው ያመለክታል፡፡
“(ረሃቡ) በራስ አቅም የሚፈታ ችግር ነው” ህወሃት
ከዜጎች ችግር በላይ ለአገር ገጽታ ግንባታ የሚጨነቀው ህወሃት/ኢህአዴግ ኃላፊነት በሚሰማዉ መልኩ ከዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመንቀሳቀስ ድርቅ በተከሰተባቸው የኢትዮጵያ ክልሎች ተገቢ ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ ችግሩን “በራስ አቅም የሚፈታ ችግር ነው” በሚል ባሳየው ዳተኝነት ድርቁ ወደ ረሀብ እንዲያድግ ከማድረግ ውጪ ይህ ነው የሚባል መፍትሄ ሲሰጥ አልታየም፡፡
ከህወሃት/ኢህአዴግ ፍላጎት ውጪ ቢሆንም አዲሱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ፤ ኢትዮጵያ የተረጋገጠባትን ድርቅ እንድትቋቋም ዓለአቀፉ ማኅበረሰብ በጋራ እንዲቆም በተደጋጋሚ ጥሪ አቀርበዋል፡፡ ያም ሆኖ ዕርዳታው በሚፈለገው መጠን ሊገኝ አልቻለም፡፡ ለዜጎች ስቃይ ደንታ ቢስ የሆነው የህወሃት አገዛዝ በዓለምአቀፍ መድረኮች የእርዳታ ጥሪ ከማቅረብ ይልቅ፤ የአገሪቱ “አዳኝ መሲህነቱን” መስበኩን ተያይዞታል፡፡ ውጤቱም የዜጎችን ነገ በማጨለም የረሀብ ቤተሰብ የሆነ ተስፋ የለሽ ትውልድ ማፍራት ሆኗል፡፡
“ልማት የረሃብ አደጋን ያጠፋል” (መለስ፣ 1887)፣
“ራሱን የቻለ በራሱ የሚቆም ከልማት ጋር ያልተቆራኝ የረሀብ ማጥፋት ፖሊሲ ያስፈልገናል” (መለስ፣ 1992)፣
“ዕድገታችን የረሀብ አደጋን ቀንሶልናል” (መለስ፣ 2004)፣
“ማንኛውንም ድርቅ ለመቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባት ችለናል” (ኃይለማርያም፣2008)፣ …
እየተባለ በህወሃት/ኢህአዴግ ሲስተጋባ የኖረው ፕሮፓጋንዳ በእዉን የማይጨበጥና የማይዳሰስ መሆኑን እየታዘብን ነዉ፡፡ በአገሪቱ “አለ” የተባለዉ “ዕድገት”ም በምግብ እህል ራስን ለማስቻልም ሆነ ከዉጭ እርዳታና ድጎማ ለማላቀቅ የቻለ አይደለም፡፡ የመንገድ እና የፎቅ ግንባታውም የድሃውን ጉሮሮ የሚዘጋ የዕለት ጉርስ ወደመሆን ሲቀየርና ህይወቱ ሲያሻሽል አልታየም፡፡ የተለመደው የድርብ አኻዝ “ዕድገት” ግን አሁንም ይደሰኮራል፡፡
ሁሌም ቢሆን ከአህዛዊ መረጃዎች ጋር የተአማኒነት ችግር ያለበት ህወሃት/ኢህአዴግ አሁንም ቢሆን በፖሊሲ መክሸፍ፣ በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በሙስናና በብልሹ አሰራሮች ምክንያት እየተባባሰ ያለውን ድርቅ ከተፈጥሮ ችግር ጋር (ብቻ) ማያያዝን መርጧል፡፡ በድርቁ የተጠቁ ዜጎችን ቁጥርም በተመሳሳይ መልኩ አዛብቶ በማቅረብ ከገባበት አጣብቂኝ ለመውጣት ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ በአገሪቱ ታሪክ ድርቅ አጥቅቶት የማያውቀው የደቡብ ኢትዮጵያ ቆላማ ክፍል በዘንድሮ ዓመት ድርቁ ከጎበኛቸው ክልሎች አንዱ ሆኖ ባለበት ሁኔታ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት አጥጋቢ ዝናብ እንዳልታየ እየታወቀ፤ አገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ርቋት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች መዳከማቸው እየታየ “አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልግቸው ዜጎች ቁጥር በእጥፍ በመቀነስ ወደ 5.6 ሚሊዮን ወርዷል” በሚል የድርቁን አስከፊ ገጽታ ለማፈን ህወሃት ጥረት ላይ ይገኛል፡፡
ከአገሪቱ ውስጣዊ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በተለየ መልኩ ያለፉት ሁለት ዓመታት እንኳንስ ተደጋጋሚ ድርቅ ለሚጎበኛቸው የኢትዮጵያ ክልሎች፤ ለመሀል አገር ከተሞችም የኑሮ ውድነቱ ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ አደባባይ ላይ የተሰጣ እውነት ነው፡፡ “የአፍሪቃ መዲና – የኢትዮጵያ ህዳሴ ተምሳሌት” በሚባልላት አዲስ አበባ በድሆች በመከበቧ ሥራ ለምግብ፤ የሆነው የሴፍቲኔት ፕሮግራም እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ ችጋሩ በዚህን ያህል መጠን አፍጦ ባለበት ወቅት ከቁጥር ጋር ድብብቆች የያዙት የህወሃት/ኢህአዴግ አመራሮች የክህደት መስመራቸውን ማጠናከሩን ተያይዘዉታል፡፡
“የአስራ አንድ በመቶ ዕድገት አስመዝግቤአለሁ” የሚለው ፕሮፖጋንዳና ተደጋጋሚ የድርቅ ዜና ዘገባዎች ያልተጣጣሙለት ህወሃት/ኢህአዴግ ማጣፊያው ቸግሮት “ድርቁን በራስ አቅም/ጥረት እንቋቋማለን” ሲል ቢቆይም፤ የድርቁን ተስፋፊነት ከመጨመር ባለፈ እንደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ባሉ ቦታዎች ድርቁ ወደ ረሃብ ደረጃ እንደደረሰ ጎልጉል ከክልሉ ያጠናቀረው መረጃ ያመለክታል፡፡ ሆኖም ራሱን የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግምባር እያለ የሚጠራው ህወሃት አሁንም “(ረሃቡ) በራስ አቅም የሚፈታ ችግር ነው” በሚለው ፕሮፓጋንዳው ገፍቶበታል፡፡
የኢትዮጵያ ሶማሌ ከድርቅ ወደ ረሀብ!
የኢትዮጵያ ሶማሌ በታወቀ ምክንያት ልዩ የሆነ የፖለቲካ ትኩረት የሚሻ ክልል ነው፡፡ ፖለቲካዊ ትኩረቱ የክልሉን ተወላጆች ወደ ማዕከላዊ መንግስት የሥልጣን ቦታ ከመሳብ ጀምሮ የክልሉን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ከመሀል አገር እንቅስቃሴዎች ጋር እየተመጋገቡ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያሳዩ በሚያስችል መልኩ ልዩ ድጋፍ ሊደረግለት የሚገባ ክልል ነበር፡፡
እውነታው ግን ከዚህ በተቃራኒው የኢትዮጵያ ሶማሌ ከኢትዮጵያ የተነጠለ ግዛት እስኪመስል ድረስ፤ የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች ለማዕከላዊ መንግስቱ ባይተዋር፣ ከኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው የተገፉ፣ በማህበራዊ መስተጋብሩ የሌሉበት፤ ዝግ ክልል ሆኗል፡፡ በዚህ የተነሳ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተወላጆች ኢትዮጵያን ያለ ፓስፖርት የሚንቀሳቀሱባት ጐረቤት አገር እንጂ አንደ አገራቸው ሲመለከቷት አይስተዋልም፡፡ ምንግዜም ቢሆን የመገፋት ውጤቱ ይኸው ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል፤ ኦጋዴንና አካባቢው በህወሃት/ኢህአዴግ እና ክልሉን በሚመራው ሶህዴፓ የተገፋና ሆን ተብሎ የተነጠለ፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣው የከፋበት፣ ለዓመታት በቀየው የርስ በርስ ጦርነት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው የደቀቀ በመሆኑ፤ ወትሮውንም የአካባቢው ነዋሪዎች ከዕለት ተረጅነት የተላቀቁ አልነበሩም፡፡ ሞት ወይም አካባቢውን ለቆ መሰደድ ዕጣ ፈንታቸው የሆነው የኦጋዴን ነዋሪዎች ለሦስት ተከታታይ ዓመታት (2007 – 2009 ዓም) በክልሉ የደረሰው ድርቅ የከፋ በመሆኑ ከቀደመው ዓመታት የባሰ የችጋር ዘመን በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አልፎም የኦጋዴን ህዝብ በህወሃት የዘር ማጥፋት የጅምላ ጭፍጨፋ ሰለባ ሆኗል፡፡
በተለይም ደገሃቡር (5 ወረዳዎች ያሉት)፣ ቆሬህ (4 ወረዳዎች ያሉት)፣ ጎዴ (7 ወረዳዎች ያሉት)፣ አፍዴር (9 ወረዳዎች ያሉት) እና የኦጋዴን አካል የሆኑ የክልሉ 4 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 25 ወረዳዎች ድርቁ እየከፋ በመምጣቱ ወደ ረሃብ በማደግ ላይ እንደሚገኝ በክልሉ ከተሰማሩ የግብረሰናይ ድርጅት ባልደረቦች ለጎልጉል የደረሰው መረጃ ይጠቁማሉ፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ባወጣው መግለጫ ከድርቁ ጋር ተያይዞ ኦጋዴን ውስጥ በተቀሰቀሰ የኮሌራ ወረርሽኝ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ሁለት ሺህ ዜጐች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ከዚህም ሌላ በቂ የህክምና ድጋፍና የመድሃኒት አቅርቦት እንደሌለ በመግለጫው ይፋ አድርጓል፡፡
ጎልጉል የአካባቢውን የመረጃ ምንጮች በመጠቀም ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገው ጥረት፤ በኦጋዴን አካባቢ የኮሌራና የተቅማጥ በሽታ የተከሰተ መሆኑንና በዩኒሴፍ ስር ያሉ የህክምና ባለሙያዎች በማዕከል (በዞን) እና በንዑስ ጣቢያዎች ደረጃ የህክምና ዕርዳታ እየሰጡ ቢሆንም፤ በገጠር ነዋሪ የሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ አለመኖሩን አረጋግጧል፡፡ እንደ ተቅማጥ ያሉ ተላላፊና ሌሎች ውሃ ወለድ በሽታዎች በዋርዴር፣ ፊቂ፣ ሊበንና ሽንሌ ዞኖች ውስጥ ባሉ 22 ወረዳዎች እንደሚታይ የጎልጉል የመረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡
በክልሉ ውስጥ ሰብዓዊ ድጋፍ በመስጠት ላይ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የእርዳታና የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅት (UNOCHA) ከአንድ ወር በፊት “Ethiopia; Activities and Resource Gap for closed Schools in Drought Affected Areas of Oromia and Somali Regions” (በኢትዮጵያ በድርቅ በተጠቁ የኦሮሚያና የሶማሊ ክልሎች በተዘጉ ት/ቤቶች ያለው የእንቅስቃሴና የሃብት ክፍተት) በሚል ባወጣው ሪፖርት በክልሉ ውስጥ 437 የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከድርቁ ጋር በተያያዘ ተዘግተዋል፡፡ 183,090 ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፡፡ ምግብና ውሃ ፍለጋ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አባወራዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ይኽው ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ እጅግ አሳዛኙ ነገር በምግብና ውሃ ፍለጋ ምክንያት ከተፈናቀሉት አባወራዎች ጋር 180,600 የሚሆኑ ታዳጊ ህፃናት እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ቁጥር ከድርቁ ጋር በተያያዘ ትምህርታቸውን ካቋረጡ ተማሪዎች ጋር ስንደምረው የክልሉን የትምህርት ሽፋን አንሸራቶ ቁልቁል የሚቀብረው ይሆናል፡፡ የአካባቢውን ሕዝብ ኑሮ ሊቀይር የሚችለው የነገው ተስፋ አሁን ባለበት ድህነት ላይ ድንቁርና ተደግሶለታል፡፡
የሶማሌ ክልል ድርቅ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት የቀጠለ ቢሆንም እንደ ዘንድሮው ዓመት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ትምህርት ቤቶች ከድርቅ ጋር ተያይዞ ተዘግተው እንደማያውቁ የሚገልፁት የአካባቢው የጎልጉል ምንጮች፤ ቀድሞውንም በዘርፈ ብዙ ችግሮች ተተብትቦ የነበረው የክልሉ የትምህርት ጥራት ጉዳይ አስታዋሽ አልባ ሆኗል፡፡ አርብቶአደር የሆነው አብዛኛው የክልሉ ነዋሪ ለእንስሳቶቻቸው ግጦሽ ፍለጋ ከቦታ ቦታ በተንቀሳቀሰ ቁጥር አብረዋቸው የሚንቀሳቀሱ ትምህርት ቤቶች /Satellite Schools/ በዩኒሴፍና በዩ.ኤስ.ኤድ ድጋፍ ሰጪነት ተቋቁመው የነበረ ቢሆንም ከድርቁ ጋር በተያያዘ እነዚህ ተንቀሳቃሽ ት/ቤቶች እና ከፊል መደበኛ ት/ቤቶች ሊከስሙ ችለዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት ድርቁን ለመከላከል ሲደረግ የነበረው ጥረት፤ የክልሉን ነዋሪዎች ከመርዳት ጐን ለጐን ለእንስሳትም የሚሆን መኖ ከማዕከል እየቀረበ የእንስሳቱን ሕይወት ለማቆየት ጥረት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም በዘንድሮ ዓመት የእንሰሳት መኖ ቸል የተባለ ጉዳይ በመሆኑ፤ ከዚህም ባለፈ በበልግ ወራት የሚጠበቀው ዝናብ ከነጭራሹ በመቅረቱ የአርብቶ አደሮች እንሰሳት ቁጥር በመመናመን ላይ ይገኛል፡፡ ለእርዳታ ምቹነት በሚል በየአካባቢው ተበታትኖ የሚኖረውን አርብቶአደር በየማዕከሉ ለመሰብሰብ በሚደረገው ጥረት እንሰሳቱ ከግጦሽ ቦታቸዉና ከወራጅ ወንዞች እየራቁ እንዲሄዱ ያደረጋቸው በመሆኑ ከመኖ እጥረቱ ጋር በተያያዘ የእንሰሳት እልቂት የሚጠበቅ ነው፡፡ እንሰሳቶቻቸውን ባጡ ቁጥር ከህይወት ሰልፍ እንደወጡ የሚቆጠሩት የክልሉ አርብቶአደሮች ቀጣይ ህልውና ምን ሊሆን እንደሚችል አሳሳቢ አድርጎታል፡፡
በእርዳታ አሰጣጥ ደንብ በየቀኑ በነፍስ ወከፍ ለአንድ ሰው 5 ሊትር ውሃ መቅረብ እንዳለበት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊና የእርዳታ ድጋፍ ድርጅት (UNOCHA) መመሪያ ይደነግጋል፡፡ ይሁንና በክልሉ ካለው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ውስንነት የተነሳ በአማካይ በነፍስ ወከፍ 2.1 ሊትር ውሃ በየቀኑ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የሚጠቁሙት የጎልጉል የመረጃ ምንጮች የውሃ አቅርቦቱ እንደ እርዳታ ማስተባበሪያ ማዕከሎች ቅርበትና ርቀት የሚወሰን መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በዚህም የተነሳ በአማካይ 2.1 ሊትር ዉሃ በተሟላ መልኩ የማይዳረስባቸዉ ቦታዎች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡
በክልሉ 18 የማገገሚያ ጣቢያዎች ተቋቁመው የምግብ እጥረት የገጠማቸዉና ከክብደት በታች ላሉ ህጻናትና ለነፍሰ ጡር/የሚያጠቡ እናቶች ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም፤ ከተረጂዎች ቁጥር አኳያ የማገገሚያ ጣቢያዎች በቂ እንዳልሆኑ በህክምና ሙያ የተሰማሩ የጎልጉል የመረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ ተንቀሳቃሽ የህክምና ቡድኖች ቢኖሩም በገጠሩ ክፍል ተዘዋውሮ የህክምና እርዳታ ለማደረግ የሚያስችል የመሰረት ልማት አቅርቦት ባለመኖሩና በክልሉ ገጠራማ ቦታዎች በተለይም በኦሮሚያ አዋሳኝ ቦታዎች የደህንነት ስጋቶች የሚታይ በመሆኑ ህክምናው በዋናነት በማዕከላት እና በንዑስ ጣቢያዎች የተገደበ ሆኗል፡፡ በዚህ የተነሳ በገጠሩ ክፍል ተቅማጥና ኮሌራ የመሳሰሉት ተላላፊ በሸታዎች ሊከሰቱ ችለዋል፡፡
ለእያንዳንዱ ሰው በነፍስ ወከፍ በወር 15 ኪሎ ግራም ስንዴ፣ በቆሎ (እህል)፣ ዘይት፣ አልሚ ምግብ ማደል የሚገባ ቢሆንም፤ እርዳታው ወጥነት ባለው መልኩ ሊደርስ አልቻለም የሚሉት የአካባቢው መረጃ አቀባዮች፤ ከዞን ከተማዎች ራቅ ባሉ ቦታዎች የሚገኙ የእርዳታ ማዕከላት እስከ ሁለት ወር ድረስ እንደሚዘገይ ይናገራሉ፡፡ ክልሉ ከማዕከላዊ መንግስቱ ራቅ ያለ መሆኑና ለሚዲያ ዝግ የሆነ ባህርይ የሚያሳይ በመሆኑ የክልሉ ድርቅ እንደታፈነ የሚያምኑ አስተያየት ሰጪዎች፤ የዚህ ሁሉ ሥረ-ምክንያት የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ውጤታማ አለመሆን የወለዳቸው ችግሮች እንደሆኑ ያምናሉ፡፡
ከድርቅ ወደ ረሃብ … ከረሃብ ወደ እርስ በእርስ እልቂት?!
በኢትዮጵያ ሶማሌ የተከሰተው ድርቅ ለተከታታይ ዓመታት ቀጣይነት አሳይቷል፡፡ የበልግ ወራት ዝናብ አለመገኘቱ፤ የውሃ እጥረት መኖሩ፤ የክልሉ መልከዓ ምድርና የህዝቡ አሰፋፈር ለእርዳታ አሰጣጥ የማይመች መሆኑ (የመሰረተ ልማቶች አለመሟላት)፤ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በበቂ ሁኔታ ለእርዳታ እጁን መዘርጋት አለመቻሉ ረሃቡን አስከፊ እያደረገው ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በተከታታይ በታዩ ህዝባዊ አመፆች በመደናገጡና የገባበት ፖለቲካዊ አጣብቂኝ ድርቁን ቸል እንዲለው በማድረጉ፤ በክልሉ ውስጥ ካለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች ጋር ተያይዞ የዕለት ምግብ ደራሽ ተረጂዎች ቁጥር ሊጨምረው እንደቻለ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፤ በቀጣይ ለድርቁ ዘላቂ መፍትሄ እስካልተቀየሰ ድረስ የክልሉ ነዋሪዎች በረሃብ መርገፋቸው አይቀሬ መሆኑን ይጠቁማል፡፡
ህወሃት/ኢህአዴግ በተደጋጋሚ እየፈፀመ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና አፈና የለጋሽ አገራትን እጅ እያሳጠረው መጥቷል፡፡ “እርዳታው ነፃ ማህበረሰብ እንዳይፈጥር ለማፈን ይጠቀምበታል” እየተባለ በለጋሽ አገራት የሚብጠለጠለው ገዢው ኃይል ለዜጎች ስቃይ ደንታ ቢስ መሆኑን ቀጥሎበታል፡፡ ከመሬት ፖሊሲው ርዕዮተዓለማዊ ስህተት የሚነሳው ህወሃት/ኢህአዴግ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ፖሊሲ ክሽፈቶች፤ በተዘጋ የፖለቲካ ሥርዓት እና ገበሬዎችን የራሱ ጭሰኛ ባደረገ ቀፍዳጅ ፖሊሲው በመቀጠሉ በቀላሉ በአገራዊ የምርት ክምችት መመከት የሚቻለው ድርቅ ወደ ረሃብ እያደገ ሲሄድ እየታየ ነዉ፡፡ ድርቁ ወደ ረሃብ ከማደጉ ባሻገር ረሃቡ ከውስን የተፈጥሮ ሃብት ቅርምት ጋር ተያይዞ ድንበር ተዋሳኝ ክልሎችን ወደ እርስ በርስ እልቂት መግፋቱ ተጠባቂ ስጋት ሆኗል፡፡
ጥቂት የሥርዓቱ ተጠቃሚዎችን የበለጠ በሃብት እያገዘፈ ብዙሃኑን ወደ ድህነትና የኑሮ ቀውስ ውስጥ እየከተተ ያለው የህወሃት በዘር ላይ ያተኮረ አፓርታዳዊ አገዛዝ በሥልጣን ለመቆየት እስከጠቀመው ድረስ ይህንን ረሃብ ለፖለቲካ መሣሪያ መጠቀሙ እንደማይቀር የራሱ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ በሶማሊ አስከፊ ጉዳት እያደረሰ ያለው ረሃብ ወደጎረቤት አካባቢዎች መዝለቁና ዜጎች የተፈጥሮ ሃብት ሽሚያ ውስጥ መግባታቸው የህወሃትን ዕድሜ እስካረዘመው ድረስ ዕልቂቱን ከማስቆም ይልቅ እንዲስፋፋ ማድረጉን ይቀጥልበት ይሆናል በማለት ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
“የህወሃት የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ፖሊሲ፤ መቀሌን እያሳደገ ጅግጅጋን በመቅበር፣ ኦሮሚያን በማድማት ትግራይን እያለማ፣ … ይቀጥላል ማለት ዘበት ነው” በማለት ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ የክልሉ ነዋሪ “እኛ አሁን “የረሃብን ጉንፋን እየሳልን”፣ እያለቀስን፣ እየሞትን ነው፤ ነገርግን የግፍ ጽዋው የሞላ ቀን የትግራዮች የብቻ ዋይታ የበዛ እንደሚሆን ዛሬ ላይ ቆሞ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል” ይላሉ፡፡ (የመግቢያ ፎቶ: በዋርዴር ወረዳ ሕዝብ ምግብና ውሃ ሲጠብቅ – በሙሉጌታ አያና/AP )
No comments:
Post a Comment