መጋቢት 12 ቀን 2009 ዓ. ም.
ከመጋቢት ወር መጀመሪያ ጀምሮ የአርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ሠራዊት አባላት በሰሜንና ደቡብ ጎንደር በህወሓት/ኢህአዴግ የአገዛዝ ሥርዓት ተቋማት ላይ የተቀናጀ የሽምቅ ጥቃት አድርሰዋል። በማክሰኝት፣ በደጎማ፣ በጯሂት፣ በደንቀዝን፣ በበለሳ፣ በአዲስ ወረዳ፣ በደንቢያ፣ አገዛዙ ቀይ ቀጠና ብሎ በሰየመው በመተማ መስመር በጭልጋ ወረዳ፤ በቆላድባ፣ አብራጂራ፣ በቸንከር ቀበሌ በአገዛዙ የፓሊስ ጣቢያዎችና የጦር ሠራዊት ካምፓች እንዲሁም ቀንደኛ የሥርዓቱ አገልጋዮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝሯል፤ በሕዝብ ላይ በደል ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ የነበሩ የሥርዓቱ ቀንደኛ አራማጆች ላይ የማያዳግም እርምጃ ወስዷል። ስለእነዚህ እርምጃዎች በወቅቱ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት ስለሆነ ዝርዝር ውስጥ መግባት አያሻም።
ይህ የፍፃሜው ጅማሮ ነው። አርበኞች ግንቦት 7 ህወሓት/ኢህአዴግን በማስወገድ ሕዝብ የፓለቲካ ስልጣን ባለቤት ለማድረግ በሚደረግ ትግል ውስጥ ራሱን ለመስዋዕትነት በግንባር ቀደምትነት አሰልፏል፤ የትግሉ ባለቤት ግን ሕዝቡ ራሱ ነው።
እስካሁን በጎንደር በተደረጉ ትግሎች የታየው የሕዝብ ንቁ ተሳትፎ አበረታች ነው። የጎንደር ሕዝብ ከአብራኩ የወጡትን የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮችን በመረጃ፣ በስንቅና በቀጥታ በውጊያ በመሳተፍ ረድቷል። ሲራቡ እያበላ፣ ሲቆስሉ እያስታመመ፣ መንገድ እየመራ ግዳጆቻቸውን በስኬት እንዲወጡ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል። በተለይ እሁድ መጋቢት 03 ቀን በጎንደር አጼ ፋሲለደስ ስታዲዮም የተገኘው ሕዝብ የአገዛዙን ዛቻ ሳይፈራ ለታጋይ አርበኛ ጎቤ መልኬ የህሊና ፀሎት ማድረጉ ለአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኗል። ሰሞኑን እየተወሰዱ ያሉትን ዓይነት የሕዝባዊ አመጽ እርምጃዎች ከጎንደር በተጨማሪ ወደ ሌሎችም የአገሪቱ ግዛቶች እንዲስፋፋ ማድረግ ይገባል።