- “ጎቤ ሲሰዋ አዳዲስ ጎቤዎች ትግሉን ተቀላቅለዋል’’
“አርበኛ ጎቤ መልኬ ተሰዋ” ሲሉ በአካባቢው የሚገኙ የጎልጉል መረጃ አቀባዮች ገለጹ። ህወሃት የሚመራው ሰራዊት ክፉኛ ጉዳት ደርሶበታል። ዜናው ኢህአዴግ በሚያስተዳድራቸውም ሆነ በሚደጉማቸው መገናኛዎች ይፋ አልሆነም። ለነጻነት ሃይሎች ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉ አካላትም ይህ ዜና እስከታተመበት ድረስ በግልጽ ያሉት ነገር የለም። አርበኛ ጎቤ እራሱን እንዳጠፋም የሚገልጹ አሉ።
በሰሜን ምዕራብ ቆላማዉ ክፍል የደፈጣ ተዋጊዎችን የሚመራዉ ታዋቂዉ አርበኛ ታጋይ ጎቤ መልኬ በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ዕዝ ስር ባለዉ “አንገረብ” እየተባለ በሚጠራዉ የስለላ ቡድንና በ“ጸረ-ሽብር ግብረ ኃይል ቡድን” የጋራ ዘመቻ በጠገዴ ወረዳ ልዮ ስሙ “አዴት” በተባለ በርሃማ ቦታ ትላንት ማምሻዉን በተካሄደ ዉጊያ ነው “ጎቤ ተሰዋ” የተባለው።
የጎልጉል የአካባቢዉ የመረጃ ሰዎች እንደገለጹት የካቲት 20 ቀን2009 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ሰዓታት ነበር ውጊያው የተካሄደው። ዉጊያ የተከፈተው ድንገት ሲሆን በከፍተኛ ኃይልና በከባድ መሳሪያ የተደራጀዉ የህወሓት የጦር ሰራዊት ድንገተኛ የማጥቃት ዘመቻ ጀመረ። በከባድ መሳሪያ ሽፋንና ሰፊ ቁጥር ባለው “ወራሪ” የታገዘው ድንገተኛ ማጥቃት በነጻነት ኃይሎች ላይ ጉዳት ቢደርስም ዱር ቤቴ ያሉት ታጋዮች ለመከላከል ባደረጉት ትንቅንቅ የህወሓት ጦር ላይ ቀላል የማይባል ጉዳትና ውድመት አድርሰዋል።
ከህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ በአርማጭሖና በጠገዴ አካባዉ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ እንዲወጣ ተደርጎ አካባቢው በህወሓት ልዩ ጦርና ዳንሻ ላይ በሰፈረዉ 44ኛ የመከላከያ ጦር ሰራዊት ዕዝ ስር እንዲወድቅ ተደርጓል። ቀደም ሲል የአማራ ክልል ፖሊስ ከለላ የሚሰጣቸው የነጻነት ሃይሎች የአማራ ክልል ልዩ ሃይል አካባቢውን እንዲለቅ ከተወሰነ በኋላ፣ ለዚህ መሰል ድንገተኛ ጥቃት ሊዳረጉ መቻላቸውን ታዛቢዎች ይናገራሉ። ትላንት ማምሻዉን ጠገዴ ወረዳ “አዴት-ጄጄ” በተባለ ቦታ የተካሄደ ዉጊያም የዚሁ ውጤት እንደሆነ የጠቆሙት ክፍሎች፣ በውጊያው የታወቁ ከሃያ በላይ የህወሓት ጦር ሰራዊት አባላትና አዋጊ መኮንን ተገድለዋል፤ ታጋይ ጎቤን ጨምሮ ዘጠኝ የነጻነት ሃይሎች ተሰዉተዋል፡፡
“ታዋቂዉ አርበኛ ታጋይ ጎቤ መልኬ በተለያዩ የሰሜን ምዕራብ ቆላማ ቦታዎች እየተዘዋወረ በህወሃት/ኢህአዴግ ኃይሎች ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ያደረሰ ጥቃት ሲፈጽም የነበረ ልበ ሙሉ ታጋይ ነበር” የሚሉት የክፍሎች “ታጋዩ ከወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተፈጠረዉ ህዝባዊ አመጽ ቤቴ፣ ንብረቴ፣ ሃብቴ ሳይል ህይወቱን ለመስጠት ምሎ የተነሳ ታጋይ ነበር’’ ብለዋል። “የጎቤን የትግል ፈለግ በመከተል እኛም የበቀል ክንዳችን እናፋፍማለን” ሲሉ የታጋይ ጎቤ መልኬ የትግል አጋሮች ቃላቸውን ማደሳቸውንም ጠቁመዋል።
“ልዩ” ከሚባለው አርበኛ መሰዋት በኋላ በርካታ ጎቤዎች መፈጠራቸውና ሰፊ ቁጥር ያላቸው ወደ ጫካ እንደሚገቡም አረጋግጠዋል። ለጥንቃቄ ሲሉ የቦታ ስሞችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። የአካባቢው የጎልጉል ምንጭ ያነጋገራቸው “ታጋይ ይሰዋል። ትግል ግን ይቀጥላል። አሁን የተጀመረው ትግል የሚቆም አይደለም። አንድ ጎቤ ሲሰዋ፣ በርካታ ጎቤዎች ወዲያው ተወልደዋል። በቅርቡ የበቀል ርምጃ ይወሰዳል። ህዝብ ተናዷል። ብሶቱና ቁጣው እየነደደ ነው። አፈናውና ስቃዩ በቃላት የሚገለጽ አይደለም። የአማራ ክልል አስተዳዳሪዎች በውክልና ህዝባቸውን የሚሸጡበት ዘመን እስኪያበቃ መስዋእትነት ይከፈላል። ጎቤ በክብር የማይቀረውን የህይወት ጉዞ ተቀብሏል። ሕዝባቸውን ለሸጡ፣ እየሸጡ ያሉና በባንዳነት የገለሙ ያካባቢው ተወላጆች ከነጌቶቻቸው ይፈረድባቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
በመጨረሻ ባገኘነው ዜና “ወራሪው ህወሃት ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም ጦርነቱን የአካባቢው ሚሊሻዎች እንዳካሄዱትና ቀላል እንደነበር በማስመሰል የፕሮፓጋንዳ ስራ ለመስራት አንዳንድ ሆድ አደሮችን ለምስክርነት አነጋግርዋል” ብለዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ከአካባቢዉ በሰበሰበዉ መረጃ መሰረት ታጋይ ጎቤ መልኬ በታች አርማጭሆ ወረዳ የተከበረ አራሽ-ነጋዴ፣ አራት የጭነት አይሱዚ መኪኖች፣ ከአራት መቶ በላይ የቁም ከብቶች፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረትና ሰፊ የሰሊጥ እርሻ መሬት ባለቤት፣ ከነጻነት በቀር ምንም ያላጣ ታዋቂ ባለሃብትና የሀገር ሽማግሌ ነበር፡፡
የአማራና የትግራይ ክልል የድንበር ይገባኛል ዉዝግብ በተካረረ ስሜት በሚራገብበት ሰዓት ችግሮች በዕርቅና በሽምግልና እንዲፈቱ ጥረት ሲያደርጉ ከነበሩ የአካባቢዉ ተወላጆች ዉስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰዉ ጎቤ መልኬ፣ በትግራይ ክልል ከፍተኛ አመራሮች አደራጅነት በየጊዜዉ በአማራ ክልል ነዋሪዎች ላይ የሚደርሰዉን ጥቃት አጥብቆ ያወግዝ ነበር፡፡ በተለይም ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ ችግሮች እየተባባሱ በመሄዳቸዉ የአካባቢዉን ችግር ለአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ባህር ዳር ድረስ በመሄድ አቤቱታ ካሰሙ ያገር ሽማግሌዎች አንዱ ጎቤ መልኬ ነበር፡፡
ይህን ጉዳይ ዛሬ ላይ በቁጭት የሚያስታዉሰዉ የታጋይ ጎቤ መልኬ የቅርብ ሰዉ “ሰዉየዉ ተገፍቶ ነበር ጫካ የገባዉ፤ የእርሱ ደም እንዲህ በዋዛ ባክኖ አይቀርም፡፡ የጎቤ መስዋዕት መሆን ከትግላችን አያሸሸንም” ሲል በመረረ ስሜት አስተያየቱን በስልክ ሰጥቶናል፡፡
የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን ለማፈን የህወሓት ጦር ጎንደር ከተማ ላይ ያደረገዉ ዘመቻ ያልታሰቡ መዘዞችን እንዳመጣበት ይታወሳል፡፡ ሐምሌ 04/2008ዓ.ም ምሽት 3፡30 ጀምሮ በየኮሚቴ አባላቱ ቤት በመዘዋወር የተካሄደዉን የአፈና ዘመቻ በመቃወም በማግስቱ ሀምሌ 05/22008ዓ.ም አደባባዩን በአመጽ የሞሉት የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችን በመደገፍ ከዳንሻ፣ ጠገዴ፣ ሶረቃ፣ ሳንጃ፣ ሙሴ ባምብ … የተዉጣጣዉን የህዝባዊ ጦር ሰራዊት በመምራት ጎንደር ከተማ ድረስ ዘልቆ በመግባት በታላቅ ጀብዱ ከህወሓት ጦር ጋር በመዋጋት የህወሓት ጦር ልዮ ኦፕሬሽን ሃላፊ የነበረዉን የዘመቻዉን ሃላፊ ኮማንደር ሀለፎም በርሄ ጨምሮ ሃያ ሰባት “የጸረ ሽብር ግብረ ኃይል ቡድን” አባላትንና አስራ ዘጠኝ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በጎንደር ከተማ ቀበሌ አስራ ስምንት አደባባይ ላይ (ኮለኔል ደመቀ ዘዉዱ መኖሪያ አካባቢ) ትግሉን ካፋፋሙት ቁንጮ የነጻነት ታጋዮች አንዱ የሆነዉ ጎቤ መልኬ በአካባቢዉ ነዋሪዎች የበዛ ክብር የነበረዉ ሰዉ መሆኑን የጎልጉል የመረጃ ምንጮች ዘገባ ያመለክታል፡፡
በስልሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ይገኝ የነበረዉ ታጋይ ጎቤ መልኬ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ ከኮሚቴ አባላቱ እስር በኋላ ተዳፍኖ እንዳይቀር የአካባቢዉን ሰዎች በማስታጠቅ ሲፋለም የነበረ ቆራጥ የነጻነት ታጋይ ነበር፡፡ የታጋዩ የቀብር ስነ ሥርዓት በታች አርማጭሆ ወረዳ “አመራ ቁስቋም” ገዳም ዉስጥ እንደሚካሄድ ከአካባቢ የደረሰን መረጃ ይጠቁማል፡፡
የታጋዩን መስዋዕት መሆን ተከትሎ ቁጣ የተቀሰቀሰባቸዉ አካባቢዎች መበራከታቸዉን የሚጠቁሙት የጎልጉል የአካባቢዉ ምንጮች ከጎንደር ወደ አርማጭሆ፣ ጠገዴ፣ ዳንሻ የሚወስዱ መንገዶች በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ዉለዋል፡፡ በየ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀቶች የመከላከያ ኬላ የተጣለ ሲሆን ዛሬ የካቲት 21/2009 ዓ.ም ከጎንደር ወደ ሁመራ የሚሄዱ መኪናዎች ከሳንጃ በኋላ በደህንነት ስጋት ጉዟቸዉ የተገታ መሆኑን ምንጮቻችን ዘግበዋል፡፡
የታጋዩ ጓዶች በጫካ ብቻ ሳይሆን በህዝብ ጥላ ስርም የታቀፉ በመሆኑ በቀጣይ የበቀል ክንዳቸዉን በህወሓት ሰዎች ላይ እንደሚያነሱ ይጠበቃል፡፡ እንደ አካባቢዉ የመረጃ ምንጮቻችን ጥቃቱ በህወሓት ሰዎች ብቻ የሚቆም ሳይሆን የህወሓት ማህበራዊ መሰረቶች ናቸዉ በሚባሉ የእርሻ ቦታዎች፣ ፋብሪካወዎችና ተቋማቶችንም ይጨምራል፡፡ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ መረረጃዎችን ከሰሞኑ የሚያደርስ ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ ዜና በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል መሳሪያ ፍታ፣ መሳሪያ ከየት እንዳመጣህ ተናገር፣ ማን አስታጠቀህ በሚሉ ጉዳዮች ሕዝብ እየታሰረ፣ እየተገረፈና እየተሰቃየ መሆኑንን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያረጋግጣሉ። መሳሪያቸውን ላለማስረከብ የሚሰወሩም እየተበራከቱ መሆኑ እየተሰማ ነው። አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ይህን ያኮረፈና የመረረው ህዝብ አደራጅቶና የትግል ስትራቴጂ ነድፎ የሚያታግል ቁም ነገረኛ ኃይል ቢኖር ትግሉ እስካሁን ብዙ ርቀት ሊሄድ ይችል ነበር።
No comments:
Post a Comment