ተሻለ መንግሥቱ
ይህ የፍዳና የሰቆቃ ዘመን እስኪያልፍና የማይቀረው ወርቃማ የነፃነት ዘመን እስኪመጣ በሰመመን የምቆይበትን ብልኃት ባገኝ ወደድኩ፡፡ እንዲያ ዓይነት ጥበብ ተገኝቶ እንደእሥራኤሉ ፕሬዝደንት (ኤርየል ሻሮል) በሞትና በሕይወት መካከል አሸልቦ ሳይሰሙ ሳይለሙ ብዙ ጊዜ መቆየት ለእንደኔ ያለው ሰው ተፈልጎ አይገኝም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የምንኖር ጥቂት የማንባል ዜጎች አብዛኛው የምንሰማውና የምናየው ነገር ግራ እያጋባን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከመኖር ይልቅ አለመኖርን እንመርጣለን፡፡ አስደንጋጭ ወቅታዊ ሁኔታ ውስጥ ተዘፍቀናል፡፡ ራሳችንን እየታመምን የምንኖር አለን – በበኩሌ በጣም እያመመኝ እንደምኖር ብደብቅ ዋሸሁ፡፡
Kinfe Dagnew (B. Gen.), the chief executive officer (CEO) of the Metal & Engineering Corporation (MetEC)
ዛሬ ጧት ነው፡፡ ከአንድ ወዳጄ ጋር እንጫወታለን – ስለወያኔዎች ሁለንተናዊ የምዝበራ ሥልትና የሙስናው ቅጥአልባነት ነበር በንዴት እየተንጨረጨርን የምናወጋው፡፡ የቀራቸው እኮ የለም፤ ሁሉንም እነሱ ተቆጣጥረውታል፡፡ በአንዲት ቀን አዳር መክበር የሚቻለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ መሆኑን ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ በተደጋጋሚ አስመስክረዋል፡፡ በአንዲት ቀን አዳር መክበር ብቻም ሳይሆን በአንዲት ቀን አዳር ማደኽየትም ሆነ አላንዳች በቂ ምክንያትና ፍትሃዊ ፍርድ አንድን ዜጋ መቅ ማውረድም እንደሚችሉ አስተዋይ ልቦና ላለው የዓለማችን ዜጋ አሳይተዋል፡፡ ላኪዎቻቸው ግን በወያኔዎች ዕኩይ ድርጊት ቢደሰቱ እንጂ አይገረሙም፡፡ እነዚህ የስቃያችን አበጋዞች ውጤቱን አስቀድመው የማያውቁትና ሲቻላቸው ደግሞ በርቀትም በቅርበትም የማይቆጣጠሩት አንድም ድርጊት በዓለም እንደሌለ የሚገነዘቡ የፕላኔታችን ገዢዎች ናቸው፡፡