Translate

Tuesday, November 29, 2016

ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ: “አገራዊ ንቅናቄው የድርጅቶች እንጅ የብሄር ውክልና የለውም”


በቅርቡ በ4 የፖለቲካ ድርጅቶች የተመሰረተው የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ትናንት እሁድ በስቶክሆልም ከተማ የተሳካ ስብሰባ ማድረጉን ገልጿል። የአርበኞች ግንቦት7 መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር መሪ አቶ ሌንጮ ለታ እንዲሁም የአፋር ህዝብ ፓርቲ መሪ ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ በስብሰባው ላይ የተገኙ ሲሆን፣ ስብሰባው በስቶክሆልም /ስዊድን የንቅናቄው አስተባባሪ አቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ ንግግር ተከፍቷል። ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ባቀረቡት ሰፊ ንግግር፣ ሁሉም የንቅናቄው አባል ድርጅቶች ኢትዮጵያን እንደ አንድ ሉአላዊ አገር የሚቀበሉ መሆናቸውን እና ችግሮቻቸውን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረት እንዳለበት ስምምነት ላይ የደረሱ በመሆኑ ተቀራርበው ለመስራት ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል። 


አገራዊ ንቅናቄው የድርጅቶች እንጅ የብሄር ውክልና የለውም ያሉት ፕ/ር ብርሃኑ ፣ ማናችንም ቢሆን ህዝበ ውሳኔ ተካሂዶ የህዝብ ውክልና ባልያዝንበት ሁኔታ የብሄሮችን ውክልና ታሳቢ ያደረገ ጥምረት ልንፈጥር አንችልም ብለዋል። ማንኛውም ድርጅት የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ከተቀበለና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመመስረት ፈቃደኛ ከሆነ በጥምረቱ ውስጥ ገብቶ መስራት እንደሚችሉ ፕሮፌሰሩ በዝርዝር አስረድተዋል።

 አቶ ሌንጮ በበኩላቸው ለብቻ የሚደረገው ትግል የትም እንደማያደርስ የ25 አመታት ጉዞ ምስክር ነው ብለዋል። ምዕራባውያንም ቢሆኑ ፍላጎታቸው እንድንሰባሰብ ነው ያሉት አቶ ሌንጮ፣ ይህ ጥምረት ረጅም ርቀት ይሄዳል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል። ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ ደግሞ “ የአፋር ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ነው “ ያሉ ሲሆን፣ በብሄር ለመደራጀት የፈለጉት አካባቢያቸው ትኩረት እንዲያገኝ እንጅ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ስትመሰረት የብሄር ፖለቲካው ያከትማል ብለዋል። ከኖርዌይ ለስብሰባ ስዊድን የተገኘው አትሌት ሙሉጌታ ዘውዴ ለውድድር ለብሶት የነበረውን የአንዳርጋቸው ጽጌ ምስል የያዘ ቲሸርትና የተሸለመውን ዋንጫ ለንቅናቄው አበርክቷል። በዝግጅቱም ከፍተኛ ገቢ መገኘቱን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment