Translate

Sunday, December 20, 2015

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባቀረቡት ጥሪ ኢትዮጵያውያን ቅድሚያ ሰጥተው ሊተገበራቸው የሚገቡ ስድስት ተግራት

አርበኞች ግንቦት 7 በሚከተሉት ስድስት ነጥቦች ዙርያ የተቀናጀ ትግል እንዲካሄድ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የትግል ጥሪ ያደርጋል።

1. በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየተካሄደ ያለው ትግል ከአሁኑ በተሻለ ተጠናክሮ እንዲቀጥል! ለዚህም በነኝህ አካባቢዎች ያለው የነኝህ ማህበረሰብ አባላት ብቻ ሳይሆን ባካባቢዎቹ የሚገኙ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ትግሉን በስፋት እንዲቀላቀሉ እንጠይቃለን! በትግሉ ሂደትም በአሮሞና በአማራ ሕዝብ መካከል የትግል አጋርነትና የግብ ተመሳሳይነት መኖሩን ማጉላት ይገባናል። በአሁኑ ሰዓት ግፉና ስቃዩ እጅግ ለበረታበት የኦሮሞ ሕዝብ “አለንልህ፣ ከጎንህ ነን” ማለትና በርግጥም ከጎኑ ተሰልፎ መገኘት ይኖርብናል።
2. በሌሎች ክልሎች ያሉ ኢትዮጵያውያን ትግሉን በያሉበት ባስቸኳይ እንዲቀላቀሉ ጥሪ እናደርጋለን! ሌሎች ክልሎችና አካባቢዎች የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች በየአካባቢያቸው ባሉ የአስተዳደር በደሎችና የነጻነት ፍላጎት ላይ ያተኮሩ እንዲሆን ማድረግ ይገባል፤ ሆኖም ግን ለአካባቢያዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት የሚቻለው የአገራችን የፓለቲካ ሥርዓቱ ሲለወጥ ብቻ መሆኑ በትግሉ ሂደት ማሳየት ይጠበቅብናል!
3. የኢትዮጵያ መከላከያና ፖሊስ ሰራዊት እንዲሁም በያካባቢው ስርዓቱን እንዲያገለግሉ የተመለመሉ ሚሊሺያዎች ከኢትዮጵያ ህዝብ አብራክ የወጡ፤ ራሳቸውም የወያኔ አገዛዝ ሰላባ የሆኑ መሆኑን ሁሌም ማስታወስ ይገባል። አርበኞች ግንቦት 7 ይህ የኢትዮጵያ ሰራዊት በወንድሞቹ፣ እህቶቹና ወላጆቹ ላይ እንይተኩስ ይልቁንም አፈሙዙን በዚህ እኩይ ስርዓት ላይ እንዲያዞር በደተደጋጋሚ ጥሪ አድርጓል፤ አሁንም በዚህ ባስራ አንደኛው ሰዓት ይህንን ህዝባዊ ጥሪ በድጋሚ እናደርጋለን! በትግሉ ውስጥ የምትሳተፉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህንን ጥሪ በየትግሉ አደባባይ ማስተጋባት፤ በጎናችን ለምናገኘው ጎረቤታችን፤ ዘመዳችን ወይንም ጓደኛችን ለሆነ የዚህ ያፈና መዋቅር አባል ሁሉ በተደጋጋሚ መንገር አንርሳ!
4. ለኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ደህዴድና ህወሓት መካከለኛና አነስተኛ ካድሬዎች እንዲሁም ዝቅተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ለሆናችሁ ሁሉ! እናንተ ዛሬ ከሕዝብ ትግል ጎን ቆማችሁ ራሳቸሁንም ሆነ አገራችሁን መታደግ የምትችሉበት ወቅት መሆኑን እወቁ። ዛሬ የሕዝብን ጥሪ ሳትሰሙ ሥርዓቱን ለመታደግ ግፍ መፈፀማቸሁን ከቀጠላችሁ ነገ ዘራፊ አለቆቻቸሁ የዘረፉትን ለመብላት ሲሮጡ እናንተን የማያስጥሏችሁ መሆኑን መረዳት ለራሳችሁም ሆነ ለቤተሰባችሁ ዘለቄታዊ ጥቅም ይበጃል። አሁኑኑ ሰልፋችሁን አሳምሩ! ነገ አብሮአችሁ ከሚኖረው ህዝብ ጋር አትጣሉ! በትግሉ ውስጥ የምትሳተፉ ኢትዮጵያውያንም ከሕዝብ ትግል ጎን ለመቆም ለሚፈልጉ ለነኝህ ወገኖች መንገዱን አመቻቹላቸው!
5. ደም እየበዛ ሲሄድ ሀሞት እየመረረ እንደሚሄድ የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ጊዜው ሳይመሽ ቢገነዘቡት ይበጃቸዋል! የኢህአዴግ ባለሥልጣናት አገራችን መመለሻ የሌለው ቀውስ ውስጥ ከመግባቷ በፊት እና የዘረፉትን ንብረት በሰላም ለመብላት በፍጹም የማይችሉበት ሁኔታ ከመፈጠሩ በፊት እየሄዱበት ያለውን የእውር ድንብር መንገዳቸውን ቆም ብለው እንዲያስቡ እንመክራቸዋለን! ለሀገራችን ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሻግር ሁሉንም ያሳተፈ ድርድር አሁኑኑ ቢጀምሩ ለራሳቸውም ላገሪቱም እንደሚበጅ ልናሳስባቸው እንወዳለን! ይህን ለማድረግ ደግሞ በቅድሚያ ሰላማዊ ሰዎች መግደልና ማፈንን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ፤ የፓለቲካ እስረኞችን በሙሉ ባስቸኳይ እንዲፈቱና አፋኝ ህጎችን በመሰረዝ ለእንዲህ አይነት ሰላማዊ ሽግግር ዝግጁ መሆናቸውን በተግባር እንዲያሳዩ እንጠይቃቸዋለን!
6. በመጨረሻም በመሳሪያም ሆነ በሌላ መንገድ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚታገሉ ኃይሎች ሁሉ እንዲሰባሰቡና ይህን ስርዓት ለማንበርከክም ሆነ በይበልጥም ከዚህ ስርዓት ባሻገር የጋራ ቤታችን የሆነችውን ኢትዮጵያ አገራችንን በእውነተኛ እኩልነት፤ በፍትህና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንደገና የምትታነጽበትን መንገድ በጋራ ለመተለም ባስቸኳይ ውይይት እንዲጀመር ጥሪ እናደርጋለን!

No comments:

Post a Comment